በሩዋንዳ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ800 ሽህ ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ፡፡

200

በሩዋንዳ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ800 ሽህ ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ፡፡

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 22/2013 ዓ.ም (አብመድ) በሩዋንዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በቦንድ ግዥና በስጦታ 807 ሽህ 781 ብር ድጋፍ በማሰባሰብ ለሚሲዮኑ ገቢ አድርገዋል።
በግድቡ ሃብት ማሰባሰብ ዙሪያ ህዳር 19 ቀን 2013 ዓ ም በኪጋሊ የኢ.ፌ.ዴሪ ኤምባሲ ከዳያስፖራ አባላት ጋር በተደረገ ውይይት አምባሳደር ሉሊት ዘውዴ ኢትዮጵያውያን ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲጠናቀቅ በታላቅ ሃገራዊ ስሜት በመነሳሳት ላደረጉት ከፍተኛ ድጋፍ እንዲሁም ሃብቱን በማሰባሰብ ለተሳተፉ የማኅበረሰብ አባላት ምስጋና አቅርበዋል።
የዳያስፖራ አባላቱ ለሃገራዊ ጉዳይ ለሚሰጡት በጎ ምላሽ እና ያላቸውን ተነሳሽነት አድንቀው ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልእክት አስተላልፈዋል።
አምባሳደር ሉሊት ዘውዴ ግድቡን መገንባት የኢትዮጵያ ተፈጥሯዊና ህጋዊ መብት መሆኑንና በዜጎች ሃብት የሚገነባና በቅርቡም ሁለት ተርባይኖቹ ስራ ሊጀምሩ እንደሆነ ገልጸዋል።
ዳያስፖራው ለግድቡ ግንባታ ተፈጻሚነት ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ኢትዮጵያውያኑም በታላቁ የህዳሴ ግድብ ድርድር መንግስት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ያከናወናቸው ስራዎች እና የተገኙ ውጤቶች የሚበረታቱ መሆናቸውን በማንሳት ወደፊትም ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በኪጋሊ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ኤምባሲ በሩዋንዳ የሚገኙ የዳያስፖራ አባላትን በማስተባበር ሃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል፤ የሚሲዮኑ ሰራተኞችም የቦንድ ግዥ መፈፀማቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ ጽሕፈት ቤት ይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
Previous articleበጎንደር ከተማ የሽብር ጥቃት ሊፈፅም የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡
Next articleበማይካድራ ህይወታቸው ያለፉ ዜጎች ቁጥር ብዛት ሊጨምር እንደሚችል ተገለጸ፡፡