
‹‹ የፈለከውን እርምጃ ትወስድብኛለህ አልመለስም፤ በእግሬ ነው የምገባው ከጦሩ ጋር›› ሌተናል ጄነራል አበባው ታደሰ
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 21/2013 ዓ.ም (አብመድ) ወንዱ ተከፋ፣ አምርሮ አዘነ፣ ሀገሩ ተደፍራበታለችና ያቺ ከነብሱ አስበልጦ የሚወስዳት ውድ እናት ኢትዮጵያ መነካቷን ሲያይ አንጀቱ ተላወሰ፡፡ ጀግኖቿ መደፈራቸውን ሲመለከት ወኔው መጣበት፣ ጠላትን ሳልደመስስ ብመለስ እኔን አያድርገኝ አለ ጄነራሉ፡፡
ገባ ጄኔራል አበባው ጠላትን ሊያባባው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድም ትህነግ ውጊያ እንደጀመረች ሶስት እንቁ ጄነራሎችን ይዘው ወደ ውጊያ ቀጣና አምርተው ነበር፡፡ ጄነራል አበባው፣ ጄነራል ጌታቸውና ጄነራል ባጫ አብረዋቸው የሄዱት ጄነራሎች ነበሩ፡፡
ሰሜን ዕዝ ጄነራል አበባው ለዓመታት የመራውና ያደረጀው ኃይል ነው፣ በውጊያ ቀጣና የነበረው ጦር ጄነራል አበባውን ሲያይ አለቀሰ፤ ምን አለ አበባው በዚህ ጊዜ ‹‹ የፈለከውን እርምጃ ትወስድብኛለህ አልመለስም በእግሬ ነው የምገባው ከጦሩ ጋር›› ነበር ያላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለዚህም ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስክር ናቸው፡፡ ጄነራል አበባው ወደኃላ አላዬም፣ በዛው አዋጋ፣ ወጋ ጠላቱን መታው፡፡
ጄነራል ጌታቸው ጉዲናም ከጦሩ ጋር አልቅሶ አልመለስም አለ፡፡ ሌትናል ጄነራል ባጫ ደበሌም አልመለስም አለ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሶስቱን ጀግና ጄነራሎች በጦር ቀጣና አሰማርተው ተመለሱ፡፡ ጄነራሎቹ ምን አሉ በዚያ ወቅት ‹‹ በፍጥነት ይህ ጁንታ ወደ ህግ እናቅርበው ከዚህ እንድታቆዩን›› ነበር ያሉት፡፡ በዚህ ወቅት ትህነግ አራት ኪሎን ለመቆጣጠር እያዛጋ ነው፡፡ የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈፀም ሀገሪቱን እንደመቆጣጠር አድርገው ነበር የወሰኑት፡፡ በጀግኖች ጥምረት በተሰራው ሥራ የትህነግ የባቢሎን ግንቦች ፈራረሱ፣ ያበጡት ኮሰሱ፣ ምሽጎች ተደረመሱ፣ ከቁጥራቸው አነሱ፣ ታዓምር የመጣ እስኪመስል ድረስ ወና ሆኑ፡፡
ትህነግ አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በትጥቅ ውጊያ በነበረበት ጊዜ ከሽራሮ መቀሌ ለመድረስ ለ15 ዓመታት ያክል ተዋግቷል፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ግን ከሽራሮ መቀሌን ለመቆጣጠር 15 ቀናት በቂው ነበር፡፡ እኛም በእግር ነው የገባነው እነርሱም በእግር ነው የገቡት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕግን በማስከበርና ኢትዮጵያን በመታደግ ዘመቻው ጀብዱ የፈፀሙትን ወታደሮች ሲጠሯቸው፡- ሳተናው ጄኔራል በላይና ልበ ቆራጡ ጄነራል መሰለ፣ በሁመራ በኩል የነበረውን የመከላከል ሥራ ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር በጥበብ ሠሩት፡፡ ትንታጉ ጄነራል አበባው በምዕራብ ግንባር ወታደሩን አስታጥቆና አደራጅቶ በርካታ ምሽጎች ይዞ ሽራሮን ተቆጣጠረው፡፡ ነበልባሉ ጀኔራል ባጫ አሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በራማና በፆረና በኩል የነበረውን ተልዕኮ ኃይል በማደረጀትና ጀምር ሲባል እንዲጀምር ተልዕኮ ተሰጠው፣ የተባለውን ከወነ፣ ጀምር ሲባልም ፈጽሞ ተገኘ፡፡
በዛላንበሳ በኩል ግስላው ጄነራል ጌታቸው የወጣውን ኃይል አደራጅቶ በከፍተኛ ጀግንነት ዛላንበሳንና አዲግራትን እንዲይዝ ተልዕኮ ተሰጠው፤ የበላይና የአበባው ጦር ሽረ ሲደርስ የባጫና የጌታቸው ጦር አካባቢውን ተቆጣጠሩ፡፡ በምሥራቅ በኩል ከባድ መሣሪያን በማስተባበር ሥራ የጀመረው ወታደራዊ ሊቁ ጄነራል ዓለምሸት ነበር ሲሉም አድናቆታቸውን ገልፀዋል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ፡፡ ከጄነራል ዓለምሸት ጋርም ነጎድጓዱ ጄነራል ሰለሞን፣ አይበገሬው ጄነራል ዘውዱ ነበሩ ሲሉም ገድላቸውን አስታውሰዋል፡፡ ሳተናው ጄነራል አበባው ከኤርትራ በነበረው ውጊያ እርሱ በሚመራው ጦርነት ቦታውን በደንብ ያውቀው ነበርና ጄነራል ጌታቸውም ዛላንበሳን ስለሚያውቅ ውጊያው በስኬት እንዲመራ እንዳደረጉትም አስታውቀዋል፡፡
ድል ቁርሱ የሆነው ጄኔራል ብርሃኑ ጁላም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ሁለት ማዘዣ ጣብያዎችን ይዞ እጅግ የሚያስደምሙ ጀግና ጄኔራሎችን በመያዝ አጠቃላይ ሂደቱን ሲመራ ቆይቷል ነው ያሉት፡፡ ከጄነራል ብርሃኑ ጁላ ጋር ሀገር ወዳዱ ጄኔራልና በሀገሩ ጉዳይ የማይደራደረው ጄነራል ዮሐንስ፣ አነፍናፊውና የጠላትን ኮቴ የሚከታተለው ጄነራል አስራት፣ ካርታን እንደ ምድር የሚያነባው የዘመቻ መኮንኑ ጄነራል ተስፋዬ፣ ሎጂስቲክስን የሚያሳልጠው ጄነራል አብዱራህማን፣ የሰው ኃይልን የሚያመጋግበው ጄነራል ሃጫሉ፣ ጄነራል ሀሰንና ሌሎችን በአንድ ኮማንድ ፓስት ስር ሆነው በሁለት ማዘዣ ጣብያ ቀንና ማታ ውጊያ ይመሩ እንደነበር ነው የተናገሩት፡፡
አርዕድ አንቀጥቅጡ የአየር ኃይል አዛዥ ጄነራል ይልማ ጀግኖቹን ተዋጊዎችን ይዞ ባሰብነውና ባቀድነው ልክ ጦርነቱ እንዲፈፀም ከፍተኛ ተጋድሎ ፈፅመዋል ሲሉም የዘመቻውን ጊዜ አስታውሰውታል፡፡
ንስሩ ጄነራል አልሹማና ጄኔራል ብራሀኑ በቀለ ልዩ ኃይሉን ( ሰፔሻል ፎርስ/ ኮማንዶው) በማደራጄት ከፍተኛ ሥራ ሥርተዋል ብለዋል፡፡ በዚህ ውስጥም የትም ዓለም ላይ የሌላ ጀግንነት ተፈፅሟል ነው ያሉት፡፡ እኔ ጀግንነት ብዬ ላዋራው የምችለው የነበር ከሌላ ጠላት ጋር ቢሆን ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገር ግን አሉ ልዩ ኃይሉ ( ስፔሻል ፎርሱ/ ኮማንዶው ) መቀሌ ላይ አንድ ሰው ሳይሞት የተቆጣጠረበት መንገድ በቃላት የሚገለፅ አይደለም በማለት ያስታውሱታል፡፡
ልዩ ኮማንዶው በሁመራ በነበረው ምሽግ አንድ ሰው ብቻ ሰውቶ ብርጌድ ማፍረሱንም አስታውሰዋል፡፡ ይህን ጀግንነት በፊልም ካልሆነ በስተቀር በእንዲህ አይነት ሁኔታ መግለፅ ይከብዳልም ነው ያሉት፡፡ ይህንን ገድል ከያንያን ሊጠቀሙበት እንደሚችሉም ገልፀዋል፡፡ በምሥራቅ በኩል የሄደው ልዩ ኮማንዶው ፊት ለፊት የሚታዬውን ጠላት አልዋጋም በማለት በሚያስደንቅ ጥበብ ውጊያውን የጀመረው ከተዋጊው ሳይሆን ከአዛዡ ላይ እንደነበርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል፡፡ በዚያ ውጊያ ጥይት ጨርሶ በእጁ ከጠላት ጋር ተናንቆ መሳሪያ የነጠቀ እንዳለም አውስተዋል፡፡
የሰባተኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ጄነራል ግርማ ክበበው ክፍለ ጦራቸው ይሞታል እንጂ መሳሪያዬን አልሰጥም በማለት ኃይሉን ይዞ ኤርትራ የገባው እርሱ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ወደ ኤርትራ ሲገባ መሸከም ያልቻለውን አቃጥሎ በመሄድ ተመልሶ ሲወጣም የተደራጄ ትጥቅ ያለው ኃይል ነበር ሲሉ ጀብዳቸውን አውስተውታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጠሉ ከዳንሻው ጀግና የአምስተኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ጄነራል ሙሉዓለም ገድል፤ ጄነራሉ ኃይል እስኪደርስለት ድረስ እየተዋጋ አንድም ትጥቅ ሳያስወስድ የቆዬ ጀግና መሆኑን አስታወሱ፡፡
በባድመ በኩል የስምንተኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ጄነራል ናስር ሙሉ ክፍለ ጦሩንና አቅሙን ይዞ እየተዋጋ ይዞ የወጣ ነው ብለውታል፡፡ እንደነዚህ አይነት ጀግኖች ኢትዮጵያ ባትፈጥር ኖሮ ሀገሪቷ አደጋ ላይ እንደነበረችም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል፡፡
የትግራይ ሕዝብ ሀገር ወዳድነትና ጀግንነት ለኢትዮጵያዊነት ያደረገው ተጋድሎ ከፍተኛ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩ የስግብግብ ጁንታና የኢትዮጵያ ጉዳይ ስለመሆኑ አሳይቷል ነው ያሉት፡፡ በየቦታውም የጁንታው ኃይል ጥሎት የፈረጠጠውን መሳሪያ ማስረከቡንና ለዘመቻው ተባባሪ እንደነበር ነው የተናገሩት፡፡
ትህነግ በጥይት ብቻ ሳይሆን በሚዲያና በዲፕሎማሲ ጦርነት ከፍታ እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንዳንድ ሀገራት ተወያዩ ብለውን ነበር፤ ነገር ግን እኛ እስክንጨፈጨፍ ድረስ ወይይት ለምነናል፣ መከላከያ ከተነካ በኃላ ግን ተወያዩ የሚሉን ሀገራት እነርሱም አያደርጉትም ይፋለሙታል እንጂ፤ ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅ ለመሆን ኢትዮጵያን ማወቅ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምንም እንኳን ደሃ ብንሆንም አንዳንድ ሀገራት ሀገር ከመሆናቸው በፊት እኛ መንግሥት የነበረን መሆናቸውን ሊያዉቁ ይገባል ነው ያሉት፡፡ ሀገርና መንግሥት ግራ የሚገባን አይደለንም ይሄን ልታውቁልን ይግባል ብለዋቸዋል የኢትዮጵያን ወዳጆች ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
እንኳን ዛሬ የዛሬ መቶ ዓመት እንግዛችሁ ብለው አይሆንም ያልን መሆናችን ከረሱ ማስታወስ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሚደራደር ሰው እንዳትጠብቁም ብለዋል፡፡
ሰላም ወዳድ መሆናችንን አውቃችሁ በትብብር አብረን እንስራ እንጂ ክብሩን አሳልፎ የሚሰጥ ኢትዮጵያዊ የለም፤ ይሄን ደግሞ አባቶቻችን ናቸው በውርስ ያሳለፉብን ብለዋል፡፡
ስጋት የሚገባችሁ ሰዎች ኢትዮጵያን ኢትዮጵያዊ እያለ ማሸነፍ አይቻልም፡፡ በክብራችን ለመጣ ለማንም አንደራደርም ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ሃገር እንዲቆይ ለመከላከያ ክብርና ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡





በታርቆ ክንዴ