
በህገወጥ ቡድኖች ላይ ቀድሞ ህግ የማሰከበር ርምጃ ለመውሰድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደነበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 21/2013 ዓ.ም (አብመድ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶክተር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው በ27 ዓመቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን አፈናና ስቃይ ኢትዮጵያዊያን እንደማይረሱት ተናግረዋል፡፡
ከለውጡ በፊት አፈናና እና በጅምላ መቅበር ለማስቀጠል፣ በርከት ያሉ ሰዎችን ተቃውሞ ለማስቀረት በገፍ እስራት ይፈፀም እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የለውጥ መሻት የሚያስቆም አልነበረም ነው ያሉት፡፡ ከለውጡ ዋዜማ የመፈንቀለ መንግሥት ሙከራ ለማድረግ ውይይት እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሲለቁ መፈንቀለ መንግሥቱ ቀርቷል ነው ያሉት፡፡
ለውጥ የጀመሩትን ለመግደል ሲታገሉ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ ይህን ሁሉ ሲያደርጉ የነበሩት መንግሥት የሚመስል ነገር ግን መንግሥት ያልሆነ አካል ለማስቀመጥ ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካ መቅረቱን ተናግረዋል፡፡
ለውጥ ከመጣ በኃላ የግድያ ሙከራ፣ የማሰር ፍላጎትና ሌሎች ፈተናዎች መኖራቸውንም አስታውሰዋል፡፡
በደሎችን ትተን በፍቅር፣ በመደመርና በይቅርታ እንተው ማለታቸውንም ተናግረዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ በደሉ ከተነሳና የበቀል እርምጃ ከተወሰደ መተላላቅ ስለሚመጣ እርቅና ሰላም ላይ እንሰራ ብለናልም ነው ያሉት፡፡
በሁሉም ከሁሉምና ለሁሉም የሆነ ሀገረ መንግሥት እንገንባ ብለን ስንነሳ ሰባኪዎች ናችሁ፤ መንግሥት ደካማ ነው ተባልን ሲሉም የነበረውን ፈተና አስታውሰዋል፡፡
ለምን ቀድሞ እርምጃ አልተወሰደም ለተባሉት ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲመልሱ በመፈለግና በማድረግ መካከል ልዩነት አለ፤ አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ በእውነተኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ የኃይል አሰላለፍ ማዘጋጄት ይገባል ነው ያሉት፡፡ የኃይል አሰላለፍ ትንተና ካልተረጋገጠ ድል ምኞት እንጂ ስኬት አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ከኃይል አሰላለፍ ባለፈም የሁኔታ ትንተና ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ሃገሪቱ በወቅቱ የነበረችበትን ሁኔታ በደንብ ያዬ ጉዳዩ ዘገዬ የሚል ጥያቄ አያነሳምም ብለዋል፡፡ አሰራሩ እጅግ አስቸጋሪ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ እርምጃ ለመውሰድ የሚቻልበት መንገድ አለመኖሩም ተናግረዋል፡፡ በወቅቱም ውሳኔ መወሰን የሚችሉ ሳይሆን ዘመናዊ እስር ቤት የነበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡ የመጀመሪያዎቹ የሥራ ወራት በመግደል፣ በመታሰርና በመታፈን መካከል የነበሩ አስቸጋሪ የስራ ጊዜ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡