“የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ስርአት ችግር ትህነግና የውንብድና ፖለቲካዊ ቀመሯ ነው” የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አብርሃም አለኸኝ

351

“የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ስርአት ችግር ትህነግና የውንብድና ፖለቲካዊ ቀመሯ ነው” የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አብርሃም አለኸኝ

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 20/2013 ዓ.ም (አብመድ) ኃላፊው በፌስ ቡክ ገጻቸው ያስተላለፉትን ሙሉ መልእክት እነሆ
የግማሽ ምዕተ ዓመት ክሽፈት የሚያወዛውዘው የወንበዴዎች ማኅበር ከሽፏል!
በድጋሜ እንኳን ደስ አላችሁ!
ሳናውቀው የሆነ፣ ሳንጠብቀው የተተገበረ ነገር የለም። ችግሩ ያለው ካለመደማመጣችን እንጂ ከከሸፈው የትህነግ የግማሽ ምዕተ ዓመት ውንብድና አይደለም። የወንበዴ ቁርሱም ሆነ ምሳው ውንብድና ነው። ምሱም ክፋትና እርኩሰት ነው። “በስርዓት ያልተመራ ሀገር ይፈርሳል” እንዲሉ ታላቋን ኢትዮጵያ በጭቆና በትር ቀጥቅጦ፣ እብደት በተሞላበት ስግብግብ ፍላጎት ከአንድ ተቋም ባነሰ ደረጃ ለባለፉት ዓመታት ያለሀፍረት አሳሯን አሳይቷታል።
እራሱን “ነጻ አውጭ” ብሎ የሚጠራው ትህነግ ጭቆናን ከዘውዳዊ ስርአቱና ከደርግ ወታደራዊ መንግስት በከፋ መንገድ ተግባራዊ አድርጎታል።
ሌሎችን ነጻ ማውጣት ቀርቶ ራሱን ነጻ ያላወጣ የአስተሳሰብ ድውይ ነው። የኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀጽ 39ን ለኢትዮጵያ ህዝብ እንደመልካም ውለታ እንቁልልጭ እያለ የብሄር ብሄረሰቦችን ህልውና ደፍጥጦ እራሱን የብሄር ነጻነትና እኩልነት ብቸኛ ጠበቃ ተደርጎ እንዲቆጠር አድርጓል። የትግራይን ሪፐፕሊክ ነፃ መንግስት ለመመስረት አቅዶ ያቆመውን አንቀጽ 39 የብሄረሰቦች ብቸኛ ዋስትና አድርጎ ለማሳየት የአዛኝ ቅቤ አንጓች የፖለቲካ ቁማር መጫወቻ ሜዳ አድርጎታል።
ከ91 በመቶ በላይ የሚሆኑ የዓለም ሀገራት የሚተዳደሩበትን አህዳዊ ቅርጸ መንግስት የክፋት ጭምብል አጥልቆ የብሄር ብሄረሰቦች ማስፈራርያ የፖለቲካ በትር አድርጎ ተጠቅሞበታል። በዓለም ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ 28 የሚሆኑ የፌዴራሊዝም ስርአት ተከታይ ሀገሮች አሉ። የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያውያን እጅግ በጣም አስፈላጊና ወሳኝ ቢሆንም ብቸኛና ተመላኪ መዋቅራዊ አማራጭ ግን አይደለም።
በፌዴራሊዝም ስርአት ተጠርንፈው ሲያበቁ የፌዴራል ትሩፋት ተጠቃሚ ያልሆኑ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች መኖራቸው አሌ ሊባል አይችልም። እነዚህ በአስር ሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች በእርግጥም የፌዴራሊዝም ስርአት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከተፈለገ ትህነግ በተንኮል የሸረበችው የህገመንግስት ድር ተበጣጥሶ መውደቅ አለበት።
እንደ አማራ ብልጽግና ፓርቲ የፌዴራል ስርአቱ ላይ የምናነሳው ተቃርኖ የለንም። የፖለቲካ ስልጣንን በእውቀት ሳይሆን በአጋጣሚ የተቆናጠጡ የፖለቲካ ሳይንስ ሽፍታዎች በግምት እንደሚዘባርቁትም የልሙጥነት ቅዠታዊ ልክፍት የለብንም። አህዳዊነት አማራጭ የመንግስት ስርአት እንጂ በደናቁርቶች መመዘኛ ተዘውትሮ እንደሚነበነበው የመርገም ጨርቅ አይደለም። የፌዴራሊዝም ስርአት ለአሁኗ ኢትዮጵያ ወሳኝና ተመራጭ እንደሆነም በቅጡ እንረዳለን። ይሁን እንጂ የትህነግ ፕሮጀክት በሆነው የፌዴራሊዝም ስርአትና ስርአቱ በወለዳቸው የሀቀኝነት መጓደል ላይ በርካታ ቅሬታዎች አሉን።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ስርአት ችግር ትህነግና የውንብድና ፖለቲካዊ ቀመሯ ነው። ትህነግ የተበተበችውን እስራት ማፍታታት ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ወሳኝ ነው። የትህነግ የውንብድና ፖለቲካዊ ቀመር የሚፈታተነው አማራውን ብቻ አይደለም። የኩናማና የኢሮብን ህዝብ ጨምሮ በቋንቋው መጠቀምና የመሬት ባለቤት መሆን እየተገባው በሸፍጥ ፌዴራላዊ ቀመር ዘውዳዊው ስርአትና የደርግ ወታደራዊ መንግስት ያላደረሰበትን ጭቆና እንዲሸከም የተገደደው የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ቀላል አይደለም።
ትህነግ የፌዴራሊዝም ስርአት አቀንቃኝና ጀማሪ ብትሆንም ፌዴራሊዝምን እራሷ በፈጠረችው ቅርጽና ይዘት እንኳን አጥብቃ ትፈራው ነበር። “የቡድን መብት ጠበቃ ነኝ” እያለች የቡድን መብትን የምትደፈጥጥ የወሮበላ ስብስብ ነች።
ይኸ በትህነግ የጭቆና ቀንበር ውስጥ የሚኖር ህዝብ የፌዴራል ስርአቱን ተቃውሞ ቢነሳና አህዳዊነትን ቢናፍቅ ነውር የሚሆነው ምኑ ላይ ነው? በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ “ፌዴራላዊ ነን” እያልን በተግባር ፊውዳላዊ አገዛዝ የምናሰፍን ከሆነ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ተቃርኖ መፍጠራችን ማጋጠሙ አይቀርም።
ለነገሩ የትህነግ የውንብድና ማኅበር ምኞቱም ሆነ ፍላጎቱ ሰፋ ሲል አድዋዊ ጠበብ ሲል ስብሀታዊ ኢምፓየርና ቫንፓየር የፖለቲካ መስመር መዘርጋት ነው። ኢምፓየሩ ሲደላደል ከኢትዮጵያ ጉሮሮ እየቀማ የራሱን ቡድን የሚያደልብ ስግብግብና ቀማኛ የወንበዴ ቲራቲም ነው። ካልተመቻትናና ከጎደለባት ደግሞ ለቀጣናው ሰላም እጅግ አደገኛ የሆነች የትግራይ ሪፐፕሊክ መንግስትን ማቋቋም ነው።
የዚህ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ኢምፓየር ስግብግብ ቡድን ጨካኝና ደም መጣጭ የሆነ ቫንፓየራዊ ባህርይ ያለው ነው። በአንድ አንድ የሆሊውድ ፊልሞች ምስል እንደምናየው የትህነግ ቡድን ቫምፓየራዊ ገጽታ ያለው ቅጥ የለሽና ለሰው አእምሮ የሚከብድ የጨፍጫፊነት ልክፍት የሚያሰቃየው ከሰይጣን ክፋታዊ መንፈስ ከፍ ያለ የክፉዎች ቃልኪዳን መረብ ነው።
ሳናውቀው የሆነ ሳንጠብቀው የተተገበረ ነገር የለም የምንለው የትህነግን የጭካኔ ጥግ በውል ስለምንረዳ ነው። “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” አይነት የአህያይቱ ፍልስፍና ነፍስ ዘርቶ አካል ገዝቶ የሚገኘው በትህነግ የክህደት አደባባይ ላይ ነው።
ለዚህ ከሀዲ ቡድን ትህነግ ስልጣን ማለት ሁሉም ነገር ማለት ነው። ትህነግ “ሁሉም ነገር ከስልጣን በታች ነው” የሚል ምስጢራዊ ስምምነት ያለው የውንብድና ስብስብ ነው። ይህ የውንብድና ስብስብ ምንጩ እንደማይታወቅ ፈሳሽ ጅረት ድብቅ ባህርይ ያለው የክፋት መልክተኛ ነው። መዳረሻው እንደማይታወቅ ወንዝ የት ቦታ ሊሰርግ እንደሚችል እንኳ መገመት የሚያስቸግር የሞራል ልዕልና የጎደለው የማይጨበጥ ንፋስ ነው።
አለ ስትለው የሚሞት ፣ ሟምቷል ብለህ ስታበቃ የሚጠጥር ምትሀታዊ መተት ነው። ከቤትህ ስታባርረው እልፍኝህ ውስጥ ተጋድሞ ፣ ከጓዳህ ስታስወጣው ባኞ ቤትህ ውስጥ ወድቆ ታገኘዋለህ። የትህነግ ቡድን ስር የሌለው ዛፍ ቢሆንም ከጎኑ ያለውን ግንድ ተጣብቆ በህይወት ለመቆየት እንደ ፓራሳይት የራሱ ያልሆነውን ምግብ ሲሻማና ሲቃማ ታገኘዋለህ።
የተሸከምከውን በግ ውሻ ነው ብለህ እንድታምን በሚያዘጋጃቸው ቃፊሮች አእምሮህን ይበርዘዋል። በሌለህበት እንዳለህ ፣ ባልኖርህበት እንደኖርህ አድርገህ እንድታምን አዚም ይጥልብሀል። አስሮ ገርፎ ካሳመመህ በኋላ ጨው እንደለመደ ጥጃ ዱካውን እንድትከተል ያስገድድሀል። የሰራብህን ደባና ተንኮል እስክትክድ ድረስ በፍቅር ይጥልሀል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት ሃምሳ አመታት የትህነግ መርዛማ ቀመር ቤተሙከራ ስለነበረች ዘርፈ ብዙ ክሽፈት አስተናግዳለች። ትህነግ በደርግ ወታደራዊ የመንግስት ስርአት ውስጥ የእልፍኝ አስከልካይ ሆና አገልግላለች። የቤተመንግስቱ ጠጅ አሳላፊ ሚናም ነበራት። የሊቀመንበር መንግስቱ ኃይለማርያም የቤተመንግስት ሹመኞችና የጸሀፌ ትዕዛዝ ጉበኖች ከትህነግ ምትሀታዊ መተት የጸዱ አልነበሩም።
ስመ ጥሩው፣ ባለጀብዱ፣ በአፍሪካ የዘመናዊ መከላከያ ሰራዊት ግንባታ ታሪክ አስፈሪና ከፍ ያለ ዝና የነበረው የቀድሞው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ምድር ጦር፣ የአየር ኃይሉ ፣ የባህር ኃይሉ በወያኔ ጦር ተፍረክርኮ እስከመበታተን ያደረሰው አንዳች መግነጢሳዊ ምትሀት ምን ነበር የሚለውን እንቆቅልሽ የሚፈታው በወገን ጦር ላይ ተከታትሎ የሚፈጸምበት የትህነግ ሴራ ወላፈን ከባድና ውስብስብ ስለነበረ ነው።
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት፣ ከእኩለለሊት አቅራቢያ በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ሉሲፈራዊ ክህደት ዛሬ የተጀመረ እንግዳ ደራሽ አጋጣሚ አይደለም። የትህነግ ኢምፓየራዊና ቫንፓየራዊ መጥፎ ልክፍት መድሀኒቱን እንደተላመደ በሽታ ሀገርና ህዝብ እየመረዘ ከቻለ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን እንደሎጥ ሚስት የጨው ሀውልት አድርጎ የማስቀረት ግብ ያለው ነው።
በኢህዴሪ መንግስት ቢሮክራሲ ውስጥ በርካታ የትህነግ ቃፊሮችና ጦፈኞች ነበሩ። ሸንጎውም ሆነ የኢሰፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅህፈት ቤት በትህነግ መናፍስት ተጠልፈው እንደወደቁ አይረዱም ነበር። የሊቀመንበር መንግስቱ ኃይለማርያም ተዋርደናል ፣ ተንቀናል ቁጭት መነሻው ውስጣዊ መገፍተር የተጫነው የመካድ ስሜት ነው። የኢህዴሪ ህገመንግስት ፣ ሸንጎውና የኢሰፓ መዋቅር ሲፈርስ ባለዝናው፣ ባለጀብዱና ባለታሪኩ የሀገር አንድነት ባለውለታው የቀድሞ መከላከያ ሰራዊት “የደርግ ወታደር” የሚል ወርደ ጠባብ ፣ ቁመተ ሲንዚሮና አመክንዮ የጎደለው ፍረጃ ተጭኖበት ያለርህራሄ በግፍ እንዲበተን ተደርጓል።
ይህ ተአምራዊ ባለዝና አብሪ ኮከብና የአፍሪካ ፈርጥ የነበረ ሰራዊት እንዳልሆነ ሁኖ ሲበታተን የትህነግ የክፋት መናፍስት የትውልዱን ስነልቦና በክሎት ኖሮ የፈጠረው ቁጭት ሰራዊቱ በነበረው ከፍታ ልክ የሚታይ አልነበረም። ይልቁንም እንደገደል ማሚቶ የሰማውን ማስተጋባት ፣ እንደበቀቀን ያዳመጠውን መድገም የተጠናወተውና አብዮት ያሰከረው የልሂቃን ስብስብ ያን በአፍሪካ ግዙፍ የሆነ ጦር “የደርግ ወታደር” እያለ ዝቅ አደረገው።
የአንድን ሀገር መከላከያ ሰራዊት ከክብር ማማ ዝቅ አድርጎ የአንድ ቡድን ጦር ማድረግ የትህነግ ሰይጣናዊ ልክፍት ነው። ደርግ የተባለው ወታደራዊ ስብስብ 120 ዝቅተኛ ባለማዕረግ ወታደሮችንና ከፍተኛ መኮንኖችን የያዘ ቡድን ሲሆን በራሱ ስም ሊጠራ የሚችል ወታደር አልነበረውም።
የደርግ ስብስብ የንጉሰ ነገስቱን ወንበር ሲነቀንቅ ሀገሪቷ የሚያኮራ ወታደራዊ ተቋም ነበራት። ደርግም ቢሆን የሀገሪቷ ወታደራዊ ተቋም አካል እንጂ ሌላ አሀድ አልነበረም። ወያኔ ስረመሰረቱ ክፋትና ጥላቻ ስለሆነ ያንን ግሩምና ድንቅ ወታደራዊ ስብስብ ወደታሪክነት ለመቀየር ሲያሴር የሀገር መከላከያ ሰራዊትነቱን ነጥቆ “የደርግ ወታደር” በሚል የኮሚቴ ስም ነው የሰየመው። ምክንያቱም ያ ኃያላን የተሰባሰቡበት ሰራዊት በወያኔ አይን ሲታይ አማራ ነው።
የትህነግ ሴራ ትህነግ እየሞተችም ሆነ ሞታ ከተቀበረች በኋላ ኑግ ውቀጡልኝ፤ በሶ አንበስብሱልኝ ፤ ዳልቻ መልክ ያላት ግንባረ ቦቃ ጠቦት እረዱልኝ ፤ ጥቁር ዶሮ አርዳችሁ አዙራችሁ ቅበሩልኝ ፤ እንሶስላ ሙቃችሁ ቅሬቱን መተላለፍያ መንገድ ላይ ጣሉልኝ ፤ ጨሌ አጥልቃችሁ፣ ረከቦት አቅርባችሁ ዕድሜ ዘመናችሁን ከድሙኝ የሚል ነው።
ትህነግ ዛሬም የትሮይ ፈረስ የማታጣ የሴራ ንግስት ናት። መቀበርያዋ እየተቃረበ በመጣበት በዚህ ሰአት አንኳን ጠረኗ ኢትዮጵያንና ህዝቧን በእጅጉ አየተፈታተነ ይገኛል። ዛሬም ጎራ ለይቶ ግጥሚያ አለ። በየቦታው በቀበረችው ፈንጂ መተማመኗን የምንረዳው የግል ንብረቶቿ በሆኑት ድረገጾቿ በምታስተላልፋቸው መልዕክት ነው። ከመቀሌ ብትፈረጥጥም የቀበሮ ዋሻ ወይም የሰነፍ ልብ ውስጥም ቢሆን ተደብቃ እንደ ሂዝቦላ ወይም ቦኮሀራም አስተሳሰቧን የምትረጭበት የሽብር ፈለግ መከተሏ አይቀርም። የትህነግ ነገር “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” ነገር ነው።
ጦርነቱን በሁሉም ክልሎች ለማድረግ የሸረበችው ሴራ ሙሉ ለሙሉ ዝግ አይደለም። አልፎ አልፎ የሚታዩ ምልክቶች ጤነኛ አይደሉም። የህግ ማስከበር ስራው ባልተጠናቀቀበት በዚህ ሰአት የድል ሽምያ ውስጥ ገብተው የሚዋዥቁ የድል አጥቢያ አርበኞችን እየተመለከትን ነው።
ትህነግ ከእነእብሪቷ ወደእንጦሮጦስ እየወረደች በምትገኝበት በመቀሌ ሰማይ ስር የምታስወነጭፋቸው ምትሀታዊ አንደርብ የቤንሻንጉል ክልልን እየረበሸው ይገኛል። በንጹሀን ሞት ላይ እየተረማመደ ከርሱን መሙላት የሚፈልገው የኃይል አሰላለፍ የዘመቻውን አቅጣጫ በመቀልበስ ትህነግን ከጣረሞት እንዳይመልሳትና ተጨማሪ የጥፋት ጊዜ እንዳይሰጣት ያሰጋል።
በኦሮምያ ክልል አብዛኛው አካባቢ ህገወጥነትን ልሱና ቅርሱ ያደረገው የትህነግ የእንግዴ ልጅ ኦነግ ሽኔ የንጹሀንን ደም እየመጠጠ እስትንፋሱን ለማቆየት መንደፋደፉ አይቀርም። ይህ ቡድን የኦሮምያ ሸለቆዎች ሲጫኑት ከጉሙዝ አማፂ ቡድን ጋር በመሆን መተከልን የሚረብሽበት፣ ንጹሀንን የሚገድልበትና ሀብትና ንብረታቸውን የደረሰ ሰብላቸውን ጨምሮ የሚዘርፍበትና የሚያቃጥልበት ስውር ምክንያት እንደሀገር የተጀመረውን ህግ የማስከበር ዘመቻ አቅጣጫውን በማሳት ሀገራችንን የሶርያና የየመን አይነት እጣ ፋንታ እንዲደርሳት አስቻይ ሁኔታ ለማበጀት ነው። መቀሌ ቢያዝም የኦነግ ሽኔ ቃልቻና ቦረንትቻ ብዙ ሰባት ይፈልጋል። ለኦነግ ሽኔ መቀሌ አልተያዘም። ለትህነግም የመቀሌ መያዝ ጉዳይ አሳማኝ አይደለም። ምክንያቱም የርዕዮተ ዓለም አምልኮት መጥፎ ልክፍት ነው። እኛ መቀሌ ተያዘች ስንል የእነሱ አእምሮ ሌላ መቀሌ በመፍጠር ይጽናናል።
ትህነግ ዛሬም በስርአተ መንግስቱ ውስጥ ያልነጠፈ ቅሬት አላት። በመላ ኢትዮጵያ ሰርገውና አድፍጠው የሚገኙ ትህነግ ሰራሽ ስልጡን የመረጃ ሰዎች በሁሉም አካባቢዎች ይገኛሉ። እነዚህ የአስተኳሽ፣ የአበላሽና የአለስላሽ ተልዕኮ የወሰዱ የትህነግ ሰዎች የትህነግ ዕድሜ ማራዘሚያ ኪኒኖች ናቸው።
የመንግስት ቢሮክራሲ ከእነዚህ የጥፋት መልዕክተኞች ነጻ አይደሉም። የፋይናንስ ተቋማት ፣ የቴሌና የመብራት ኃይል የቴክኒክ ሳሎኖች፣ የነዳጅና የወጭ ገቢ ትራንስፖርት መዳረሻዎች ፣ አለም አቀፍ የሚዲያና የኢትዮጵያ አለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ተቋማት፣ አየር መንገዳችንን ጨምሮ አብዛኛው የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት በብዙ አስርተ አመታት የተተበተቡ የሌጊዎናውያን (የአጋንንት ስብስብ) ጥምረት ማዕከላት ናቸው።
እነዚህ የትህነግ ኢምፓየርና ቫንፓየር ክፉ መልዕክተኞች በአስተሳሰብና በተግባር ወዳጅነት የተጣመሩ አንዳቸው ለሌላቸው መጋቢ ሚና ያላቸው የግማሽ ምዕተአመት ክሽፈት የሚያወዛውዛቸው ደመጠጭ ስብስቦች ናቸው።
በአስተሳሰብ ትህነግን እንጸየፋለን የሚሉ በተግባር የትህነግ ደጋፊዎች የሆኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ቀላል አይደሉም። የትህነግ የእንግዴ ልጆች ከሆኑት ኦነግ ሽኔና መሰል ተላላኪዎች በተጨማሪ ጸረ ትህነግ አቋም ያላቸውን የሀገር ዋልታና ምሰሶዎች ለማፍረስ የሚያቅዱና የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች የትህነግ የእድሜ ማራዘምያ መፍትሄ ስረይ ናቸው።
በዚህ ወቅት የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን፣ ልዩ ኃይላችንና ሚሊሻችን ጠንካራ ውህደትና ቅንጅት ያስፈልጋቸዋል። በተመሳሳይ የህግ ማስከበር ዘመቻውን በበላይነት የሚመሩት የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ አዛዥ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በየደረጃው ያሉ የገዥው ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችና የጦር ጀኔራሎች፣ ከጠላት ኃይል ጋር ፊት ለፊት እየተፋለሙ ያሉ የመከላከያ ሰራዊት፣ የልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት እንዲሁም ታላቋ ሀገራችን ኢትዮጵያ ወቅታዊና አስቸኳይ እገዛና ድጋፍ ይፈልጋሉ።
የተጀመረው ሀገር የማዳን ዘመቻ በስኬት መጠናቀቁ አይቀርም። ይሁን እንጂ ጥሎብን የሚያልፈው የቤት ስራ በዋዛ የሚታይ አይሆንም። የትህነግ ቅሪቶች የወደፊት አቅጣጫም በውል አይታወቅም። ትህነግ የቦኮሀራምን መንገድ ትከተላለች ወይስ እንደ አይ ሲስ ኦነግ ሽኔንና መሰል ጽንፈኞችን አሰባስባ በሽብር ተግባር ትጠመዳለች የሚለውን ቢሆነኝ (scenario) መፈተሽና የቀጣይ መፍትሄዎችን ከወዲሁ ማበጀት ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግ የተማረ ልብ ፣ የተዘጋጀ ህሊናና ኢትዮጵያዊ ቅን ልቦና ይዞ ለሀገርና ለህዝብ በወትሮ ዝግጁነት የቆመ የኃይል አሰላለፍ ያስፈልጋል።
ከዚህ ተነስተን ምን እናድርግ !?
1. መስዋዕትነት አንድ ያደረጋቸውንና ያዋሀዳቸውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት የልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላትን አንድነት ከሚያበላሽ ግብታዊ ተልዕኮ በመቆጠብ የዘመቻውን ስኬታማነት እናረጋግጥ።
የተጀመረው ህግ የማስከበር ስራ የሁሉንም መስዋዕትነት የጠየቀ ወሳኝ መድረክ ነው። በዚህ መድረክ በሁሉም ወገን አስገራሚ ጀብዱ ተፈጽሟል። አንደኛው ለሌላኛው ሽፋን ሰጥቶ ተሰውቷል። አንደኛው ሌላኛውን ከገባበት የሞት አጣብቂኝ ክቡር መስዋዕትነት ከፍሎ ህይወቱን ከማጥ ታድጎለታል። የተከፈለው መስዋዕትነት ኢትዮጵያን የሚያጸናና የሚጠብቅ ፣ ትህነግ ከጋረጠችብን የመበታተን አደጋ ፈልቅቆ የሚያወጣ ነው። የደም ትንሽ ፣ የህይወት መስዋዕትነት ስስ የለም።
ሁሉም ለተመሳሳይ አላማ ተዋድቀዋል ፤ እየተዋደቁም ነው። ሁሉም የማይናቅ ተሳትፎ ፣ አስደማሚና አስገምጋሚ የጦር ውሎ ጀብዱ አላቸው። ይኸ ፍልሚያ የጎዳና ላይ ትዕይንት ወይም ታላቅ ሩጫ አይደለም። ህይወት የሚከፈልበት የሀገርና የህዝብ ፍቅር የመስዋዕትነት መድረክ እንጂ። ስለሆነም አንዱን ከፍ ሌላውን ዝቅ የሚያደርግ የካቲካላ ቤት ፍልስፍና በማቆም ድላችንን በጋራ እናጣጥም።
ታሪካችንን ከባለታሪኮች እየተቀበልን በየአውዱ እንሰንድ። የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኔ ፣ የአንተ ፣ የአንቺና የሁላችንም ባለውለታ ነው። ልዩ ኃይላችንና ሚሊሻችንም እንዲሁ። ሀገራዊ አላማና ክቡር መስዋዕትነት አንድ ያደረጋቸውን በአሉባልታ መለያየት የትህነግን የሴራ ጡጦ ተቀብሎ በስስት እንደመማግ ያለ እርግማን ነው።
2. የሀገራችን የቅርብና የሩቅ ሁኔታ በተጨባጭ ምን ሊሆን እንደሚችል እርግጠኛ መሆን አንችልም። ስለሆነም የተጀመረውን ህግ የማስከበር ዘመቻ ከማደናቀፍ ማንኛውም አይነት ሙከራ ታቅበን ገንቢ ድጋፋችንን እናረጋግጥ።
በዘመቻው በመሳተፍ የህይወት መስዋዕትነት መክፈል ባንችል ቢያንስ ዘመቻውን ከማደናቀፍ እንታቀብ። ይኸ ዘመቻ ሽዎች መስዋዕትነት የሚከፍሉበት ዘመቻ ነው።
በትህነግ ግፍ ተጨፍጭፈው ፣ በሰይፍ ተቀልተው ፣ በጩቤ ተወግተውና በሲባጎ ታንቀው ፣ በክላሽና በቡድን መሳርያ ተደብድበው ፣ በየቤተ እምነቱ ለአገልግሎት በቆሙበት ተቃጥለው ፣ ለበድነ ስጋቸው እንኳ የሚራራላቸው ልብ አጥተው ዛፍ ላይ ተንጠልጥለው ፣ በመኪና ተጎትተው የአራዊትና የአሞራ ሲሳይ የሆኑ፣ ከሚማሩበት ቀየ ታፍነው ተወስደው ለወላጅ ዘመዶቻቸው የልብ ስብራት ምክንያት የሆኑ ፣ ሀገር ሰላም ብለው በተቀመጡበት ድንገተኛ ከበባ ተፈጽሞባቸው በግፍ ተጨፍጭፈው ህይወታቸው እንዲያልፍ የተደረጉና በጅምላ የተቀበሩ፣ መቀበርያ ስፍራ ተከልክለው በገዛ ቀያቸው በየጉድጓዱና በየጉድባው ተወርውረውና እንደቆሻሻ ታጭቀው ለተገኙ ወገኖቻችን ሰቆቃ በሙት መንፈስ የፍርድ መሻት ጉጉት ውጤቱ በድል እንዲቋጭላቸው ይፈልጋሉ በሚል ከፍ ያለ የሞራል ልዕልና ልናግዛቸው ይገባል።
ይህንን ዘመቻ ከማደናቀፍ በላይ የትህነግ ግልሙትና ተጠቂ መሆን ከየት ይገኛል። ስለሆነም የማህበራዊ ድረገጽ ስካራችንን እናብርደው። ወዲያና ወዲህ ተሰልፈን የምንፈጽመውን የጨቅላ ፖለቲካ እናቀዝቅዘው። አጋጣሚውን ለተራ ፍላጎትና እርካሽ ጥቅም ለማዋል የምናደርገውን ግብ ግብ ለጊዜውም ቢሆን እንቆጣጠረው።
3. መሪዎችን እናግዛቸው ፤ ማገዝ ባንችል እንኳን አናደናቅፋቸው።
ይኸ የታሪክ መድረክ ለመስዋዕትነት የተዘጋጀ ደፋር ፣ ትጉህና አዋቂ መሪ ይፈልጋል። መሪነት ሳይንስም ጥበብም ነው። ሳይንስ የመሪነት አስኳሉ ሲሆን ጥበብ ደግሞ ውበቱና ጣዕሙ ነው። ሳይንስንም ጥበብንም ባለመጫማት የትህነግን መብረቃዊ ጥቃትና ምትሀታዊ መተት መቋቋም ከቶ አይቻልም።
ትህነግ የግማሽ ምዕተአመት ክሽፈት የሚያወዛውዘው የወንበዴዎች ማህበር የኪሳራ ታሪክ ያላት ቢሆንም ኪሳራዋን ያወረሰቻቸው የፖለቲካ ኃይሎች የጥፋት መንገዷን ሲከተሉ ከማየት በላይ አሳፋሪ ድርጊት የለም።
እነዚህ የትህነግ ጥባቴዎች ከህዝብ መሪዎች ጋር የማይታረቅ ተቃርኖ አላቸው። የትህነግ የመጀመርያው የከሸፈ ሴራ የሀገርና የህዝብ መሪዎችን በመምታት ከፍ ሲል የኢትዮጵያን ዝቅ ሲል የአማራን ህዝብ ማዋረድ ነበረ።
“እረኛውን እመታለሁ በጎችም ይበታናሉ ” እንዲል ታላቁ መጽሀፍ መሪዎችን በመምታት የህዝቡን ተስፋ ማጨለም የትህነግ አምልኮት የማይታረቅ ተቃርኖ ነው። ይህንን መሰል የጥፋት መንገድ ለመከተል የሚዳዳቸው አልፎ አልፎም ዝግጅት የሚያደርጉ የእልፍኝ አስከልካዮች የመረጡት መንገድ ፍጹም የተሳሳተ መሆኑን አውቀው ህዝባቸውን ዳግም እንዳይበድሉ ማረቅ ያስፈልጋል። የትህነግ አላማ እስካልሞተ ድረስ ትህነግ ተቀብራለች ወይም ልትቀበር ነው ብሎ የሆማ ቅጠል መዘንጠፍ ያለቀለት የተሳሳተ ድምዳሜ ነው። እርግጥ ነው በፈጣሪ ቸርነት የተመራው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የወንበዴው በድን ራስ ገዝ የሆነችው የሰሜኗን ኮከብ መቀሌን (head quarter) በ19/03/2013 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር ማድረግ ችሏል። ይኸ ግን የድል ጉዞ ጅማሬ እንጂ ፍጻሜ አይደለም። ስለሆነም መሪዎቻችንን እናግዛቸው ማገዝ ባንችል እንኳ አናደናቅፋቸው።
4. ትህነግ ባለማተቡንና ጀግናውን የቀድሞ መከላከያ ሰራዊት “የደርግ ወታደር” ስትል አሸማቃ መዋቅራዊ የስነልቦና ጥቃት ፈጽማባቸዋለች። አማራን ትምክህተኛ፣ ነፍጠኛና የቀድሞ ስርአት ናፋቂ በሚሉ ፍረጃዎች ከከፍታ በማውረድ ተጠርጣሪና በሁሉም መስክ ተሳዳጅ እንዲሆን አድርጋለች። የብልጽግና ፓርቲን በተለይም የአማራ ብልጽግና ፓርቲን “አህዳውያን” ወይም “ትምክህት አፈር ልሶ ተነስቷል” እስከማለት የደረሰ የፌዝ ስንኝ ቋጥራለች። አንድን ነገር መፈረጅና ከከፍታ ዝቅ ማድረግ የትህነግ የመሪን አከርካሪ የመምታትና ሞተር ቤቱን (power house ) የማቃጠል የትግል ስልት ነው። ትህነግ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን “የፋሽስቱ አብይ ወታደሮች” ስትል በይፋ ተሳልቃለች።
የኦነግ ኃይሎችም የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ሲያጣጥሉ ” የአብይ ወታደሮች ” ይሏቸዋል። እንዲህ አይነት አሰያየም የጠላት በትር ልስ ከመሆን ያለፈ ትርፍ የለውም።ስለሆነም የአማራን ልዩ ሀይልም ይሁን የአማራ ሚኒሻ ከአማራ ህዝብ አብራክ የተገኙ የቁርጥ ቀን የህዝብ ልጆች መሆናቸውን አፅኖኦት ሰጠን በሚገባቸው የወል እና የክብር ስም በመጥራት የትህነግን መንገድ ባለመድገም ስህተት ከመስራት ልንቆጠብ ይገባል።
አንድን ነገር በቅን ልቦና መጠየቅ ያስፈልጋል። ስልጣን ቀሪ ነው። ህዝብ ከፖለቲከኞችም ፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎችም በላይ ነው። የተጀመረው ዘመቻ በድል ከተጠናቀቀ በኋላ ሁላችንም በህዝቡ ፊት ለፍርድ እንቆማለን። ያኔ ወይ ስልጣን እንያዘለን። ወይ ተፎካካሪ ፓርቲ እንሆናለን። ከዚህ መለስ ያለው ፍጥጫ ስለማይጠቅመን እርስ በእርስ መፈራረጁንና መጠላለፉን ትተን ለኢትዮጵያ መቀጠል እጅ ለእጅ እንያያዝ።
ድል ለሀገር መከላከያ ሰራዊታችን !
ድል የኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት መከበር የጀርባ አጥንት ለሆነው ለአማራ ልዩ ኃይል !
ድል ሁሌም በሀቀኛ የህዝብ መድረክ ቀድሞ ለሚገኘው ለአማራ ሚሊሻ !
ጉዟችን ወደቀደመ ከፍታችን !
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ !
Previous article‹‹ታሪክ የደገሙ የአባቶቻቸው ልጆች››
Next articleየኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ ልዩ ስብሰባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡