‹‹ታሪክ የደገሙ የአባቶቻቸው ልጆች››

698

‹‹ታሪክ የደገሙ የአባቶቻቸው ልጆች››

ባሕር ዳር: ኅዳር 20/2013 (አብመድ) ተኩሰው አይስቱም፣ ከኢላማ ውጭ አይመቱም፣ ለሞት አይሰጉም፣ ከጉድብ አያፈገፍጉም ‹‹እንኳንስ በቀን ቢሆን በማታ ግንባሩ ላይ ነው ለይቶ የሚመታ›› ተብሎላቸዋል፡፡ ለነጻነት ሲሉ ወድቀዋል፣ ለነጻነት ሲሉ የደስታ ህይወት ትተዋል፡፡ ሀገር ተነካ፣ ወገን ተደረፈ ሲባሉ ‹‹ጥራኝ ጫካው ጥራኝ ዱሩ፣ ላንተም ይሻልኻል ብቻን ከማደሩ›› ብለው ጠላት ሳይመለስ፣ ትቢያ ሳይለብስ፣ ክንዳቸውን ሳይቀምስ አንመለስም ብለው ይዘምታሉ፡፡
ቃላቸውም ክንዳቸውም አይታጠፈም የልባቸውን ሰርተው፣ ወገናቸውን አኩርተው ነው የሚመለሱት የአማራ አርበኞች፣ የአሁኖቹ ልዩ ኃይልና ሚሊሻዎች፡፡
ተሰማ ሀብተ ሚካኤል በመዝገበ ቃላቸው ዐማራ የሚለውን ቃል ዐማራ፣ ዐምሓራ ‹‹የተመረጠ፣ ነጻነት፣ ትውልድ ያለው ሕዝብ ነው፡፡ ዐም፣ ሕዝብ፣ ሐራ፣ ሑራ የወጣ፣ ጨዋ፣ ነጻነት ያለው ወገን ወይም አሸናፊ፣ ድል ነሺ ማለት ነው ›› ብለውታል፡፡
ነጻነትን በሥሙ ጭምር የተጎናፀፈ ሕዝብ ስለ ስሙ ክብር ይሞታል እንጂ እጁን ለጠላት አይሰጥም፡፡ አማራ ችኩል አይደለም በሆነው ባልሆነው አይገነፍልም፣ ጨቋኝ አይደለም የሰው መበት አይነካም፣ ድንበር አይገፋም፣ በሰፊ ምድር አይጠብም፣ ከሰው ዘር መሃል ዘር አይመርጥም፤ ለእናት ሀገሩ አይለማመጥም፤ የፈጣሪን ቁጣ በፀሎት፣ የጣላትን በትር በጥይት የሚመለስ ነው፡፡
አማራ ሕግ አክባሪ፣ እውነት መስካሪ፣ ለቃሉ ኗሪ፣ ለሀገሩ ፍት አውራሪ ነው፡፡ ከፀብ በፊት እርቅ፣ ከጉዞ በፊት ስንቅ ይቅደምም ይላል፡፡
‹‹በባንዴራው አምላክ፣ በሕግ አምላክ›› ከተባለ እግሩን አያነሳም፡፡ ኢትዮጵያን ከነብሱ በላይ ይወዳታል፡፡ ለዚያም ነው ከአንቺ በፊት እኔን ያድርገኝ እያለ ሲዋደቅላት የኖረ፣ እየተዋደቃላት ያለ፣ የሚዋደቅላት፡፡
በሕግ አምላክ ተብሎ በእርቅ ተጠይቆ አሻፈረኝ ያለው ጠላት ግን ወዮለት፣ በነጻነት ጠባቂዎቹ አፈሙዞች ይቀጣል፡፡ አማራን ቀበርነው ሲሉት የሚነሳ፣ አሸነፍነው ሲሉት ድል የሚነሳ ነው፡፡ ኢትዮጵያን በልቡ ቀርፆ ለዘላላም እንዳትጠፋ አስቀምጧታል፡፡ በኢትዮጵያ የመጣበትን በሙሉ በአፈሙዞቹ ገርፏቸዋል፡፡ ስለ ኢትዮጵያ እንኳን ሰው የተዋደቀባቸው ተራራዎች፣ ሸንተረሮች፣ ዱርና ገደሎች ሁሉ ይመሰክራሉ፡፡
በአድዋ ተራራ እንዳልነበረች ሆና ለወሬ ነጋሪ ያልተመለሰችው ጣልያን ለዓመታት ሴራ ሸርባ ዳግም ወደኢትዮጵያ ተመለሰች፡፡ ምንም እንኳን እንደ አድዋው ሁሉ በአንድ ጀንበር ባትመለስም ለአምስት ዓመታት በባሩድ ምጣድ ተቆላች፡፡ በየደረሰችበት ሁሉ የእሳት ራት እየሆነች ስትቀር የኢትዮጵያ አርበኞች፡-
‹‹ጀግናው ሲመጣ ሎጋው ሽቦዬ፣
ጎበዝ ሲሰለፍ ጊዜ እየለዬ፣
የጫረው እሳት ሲፈጀው ታዬ፡፡›› አሏቸው፡፡
ገፍቶ አይሄም እንጂ ገፍተው ከመጡበት ከእጃቸው ያለውን ሁሉ እየነጠቀ አይቀጡ ቅጣት ይቀጣቸዋል፡፡ ነጻነት ጠባቂ አፈሙዞች ትናንት አሸንፈዋል ዛሬ እያሸነፉ ነው፡፡ ነገም ያሸንፋሉ፡፡ አማራን ለማጥፋት የአርባ ዓመት ዕቅድ ነድፋ የመጣችው ጣልያን አማራውን አጥፍታው ሳይሆን አጠንክረው ነው የተመለሰችው፡፡ የራሷን ታሪክ አርክሳ የአማራንና የመላውን ኢትዮጵያዊ ታሪክ አንግሳ ነበር የተመለሰችው፡፡ ባልነበረ በደል በሌለ ታሪክ ተነስቶ አማራን ለማጥፋት ለዓመታት የተነሳችው ትህነግ አማራውን አጠንክራ እራሷ የሞት አፋፍ ላይ ደርሳለች፡፡
ቹቹ አለባቸው ‹‹ዳገት ያበረታው የአማራው ፍኖት›› በሚለው መጻህፋቸው ‹‹አማራ ነጻነት ያለው አሸናፊና ድል አድራጊ›› ነው ይላሉ፡፡ አማራን ዳገት እንደሚያበረታው እንጂ እንደማያደክመውም አፅንዖት ሰጥተውበታል፡፡
የአማራ ልዩ ኃይል ጋፋት ብርጌድ ሁለተኛ አባ ናደው ሺህ አለቃ አዛዥ ሺህ አለቃ ደጀኔ ማሩ አማራ የሚዋደቀው ለአንድነትና ለሀገር ነው፣ በኢትዮጵያዊነቱ ተማምኖ ነው የሚንቀሳቀሰው፤ አማራ ጎጠኝነትን አያቀነቅንም ይሉታል፡፡ አማራ በኢትዮጵያና ስለኢትዮጵያ የተፈጠረ ሕዝብ ነው፤ የሚያምነውም ከቀስተ ደመና በወሰዳት በቃል ኪዳኗ አንዲት ሰንደቅ አላማ ነውም ነው ያሉኝ ሺህ አለቃ ደጀኔ፡፡
አማራው አይሸነፌነትን፣ አርበኝነትና ጀግንነትን ከአባቶቹ የወረሰውና የታደለው ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡ አማራው ለኢትዮጵያዉነትና ለአንድነት ስለሚታገል ያለው ይሳካለታል፣ ዘምቶ ያሸንፋልም ነው ያሉት፡፡ አማራ ወራሪን የሚያሳፈር፣ አንድነትን የሚያጠናክር በኢትዮጵያዉነት የማይደራደር ነው፣ የአሁኖቹ ልጆቹም የአባቶቻቸውን ታሪክ እየደገሙት ነው ብለውኛል፡፡ በአማራነት፣ በክብርና በኢትዮጵያዊነት ድርድር ብሎ ነገር የለምም ነው የሚሉት ሺህ አለቃው፡፡
የትህነግን ሰሬኝትና ዘረኝነት በመረዳት ትግል የጀመሩት በ1987 ዓ.ም እንደሆነም ሺህ አለቃ ደጀኔ ማሩ ነግረውኛል፡፡ ህልማቸው የአባቶቻቸውን አደራ ማስመለስና በትህነግ የግፍ በትር በጨለማ ውስጥ የተዘጉትን ንጹሃንን አውጥቶ ብርሃን ማሳዬት ስለመሆኑም ነግረውኛል፡፡
ትህነግ እንደዛሬው መውጫ በሯ ሳይጠብባት ሺህ አለቃ ደጀኔ ማሩን በሕይወቱ ላይ ሶስት አማራጮችን ሰጥታ እንደነበርም ነግረውኛል፡፡ ‹‹አንደኛ ወደ መሀል ሀገር ገባ በልና የፈለከውን እናድርግልህ፣ ሁለተኛ ሚስትና ልጆችህን ይዘህ ወደ አሜሪካ ሂድ በዚያም የሚቀበልህ ሰው ይመቻችልኃል፣ በዚያ ሰርተህ ኑር፣ እዚህ አፍንጫችን ሥር ተቀምጠህ ድንበር እያልክ አታውክን ፤ ይሄን ባታደርግ ግን ልጆችህን ሳታሳድግ ትቀራለህ እንገድለኃለን›› ነበር ያሏቸው፡፡
የሺህ አለቃው መልስ ‹‹ማንነት በገንዘብ አይለወጥም፤ ገዳይ እግዚአብሔር ነው፣ ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይደንም፣ እስከ አፍንጫችሁ ብትታጠቁም መግደል አትችሉም›› የሚል ነበር፡፡ ትህነግ አደኗን ቀጠለች፤ ሺህ አለቃውም ጥንቃቄያቸውን አጠናክረው ትግላቸውን ቀጠሉ፤ እገድላለው ብላ የነበረችው ትህነግም በሺህ አለቃውና መሰሎላቸው የጠና ትግል ከመግደሏ አስቀድሞ ሞቷ ተፋጠነ፡፡ በትግሉም የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ የተሞከረበትን ጥቃት በመመከትና በማጥቃት ያባቶቹን ታሪክ ነው የደገመውም ብለዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ በጀግንነቱና በታማኝነቱ አንቱታ ያተረፈውን የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በሀገሩ ላይ ክብሩ መደፈሩንም ተናግረዋል፡፡ ይህ የሀገር ኩራት የሆነውን መከላከያ ሠራዊት ሲነካ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ የጁንታውን ቡድን ትጥቅ እያስፈታ፣ እየማረከና እየደመሰሰ መከላከያ ሠራዊቱን ታድጓል ነው ያሉት፡፡ ታላላቅ የጦር መሳሪያዎችን በማስጣልና በመማረክ ጀብዱ መፈፀማቸውንም ተናግረዋል፡፡ በትግሉ ከፍተኛ የሆነ የአማራነትና የኢትዮጵያዊነት አኩሪ ታሪክ መመዝገቡንም ነግረውኛል፡፡
የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ለአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም የሚያኮራ ነው ያሉት ሺህ አለቃ ደጀኔ የተሠራው ጀብዱ እጃቸውን ለሚቀስሩ የውጭም የውስጥም ጠላቶች ትምህርት ነው ብለዋል፡፡ ልዩ ኃይሉና ሚሊሻው ማንንም የማይፈራ፣ ከጀግናው መከላከያ ሠራዊት ጎን በመሆን አኩሪ ታሪክ የፈፀመ፣ ነገም በአንድነቱ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ነው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያን ለመውጋት እሳት የሚጭር ካለ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር በመሆን አይቀጡ ቅጣት የሚቀጣ፣ የአባቶቹን ታሪክ ያደሰ፣ ነገም ታሪክ የሚሰራ ነው ብለዋል፡፡
ትህነግ የእጁንና የስራውን እያገኜ እንደሆነ የተናገሩት ሺህ አለቃ ደጀኔ ማሩ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለህግ እስኪቀርብ ድረስ በጋራ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ለኢትዮጵያ ክብር ሲል ነው የተሰዋው፣ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች እኛ በአንድነት ሆነን ኢትዮጵያን መጠበቅና ማስቀጠል አለብን ነው ያሉት ሺህ አለቃው፡፡
ሴረኛዉ ትህነግ በፈጸመው ክደት የመከላከያ ሠራዊት ከአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ጋር በመሆን ቀጥተውታል፡፡ የፎከረባት ምድር ጠበዋለች፡፡ ግፍ የሰራባት ጀንበር ናፍቀዋለች፡፡ ይመኩበት ውሸት፣ ያስፈራሩበት ብረት ከእጃቸው ርቋል፡፡ በእነርሱው የተሰሩት የግፍ እስር ቤቶች ተከፍተው ሰሪዎቻቸውን ለመቀበል የተዘጋጁ ይመስላል፡፡ ትክክለኛው ቤት ትክክለኛውን ቤተኛ ለመያዝም እየጠበቀ ነው፡፡
ነጻነት ጠባቂ አፈሙዞች አይታጠፉም፣ በፍቅር የመጣ በፍቅር በፀብ የመጣን በጦር መመለስ የኢትዮጵያዉያን መገለጫ ነው፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article‹‹ኢትዮጵያ ማቋን አወለቀች››
Next article“የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ስርአት ችግር ትህነግና የውንብድና ፖለቲካዊ ቀመሯ ነው” የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አብርሃም አለኸኝ