‹‹ኢትዮጵያ ማቋን አወለቀች››

292

‹‹ኢትዮጵያ ማቋን አወለቀች››

ባሕር ዳር: ኅዳር 20/2013 (አብመድ) የጭንቅ ዘመን ያለፈ ይመስላል፣ የአማራ የደም ቦዮች ይደርቃሉ፣ እውነት ይፈርዳል፣ ሕዝብ እና ሕዝብ ይዋደዳል፡፡ ለዓመታት ጥላ ያጣለችው ፀሐይ ያለ ከለላ ልትወጣ ወጋገን የታዬ ይመስላል፡፡ እነሆ በጉድጓድ የተጀመረው በጉድጓድ ተጠናቋል፡፡ ሲመጡም በጉድጓድ ሲሄዱም በጉድጓድ ሆኗል ሥራቸው፡፡ ከጥይት ያልወጣ አስተሳሰብ የሕልሙ መጨረሻ በጥይት ይቋጫል፡፡
ለዓመታት የተዘጋጄው የጦርነት ድግስ አንድ ወር እንኳን እንግዳ አልሸኜም፡፡ ዳሱ ባዶ ሆኗል፣ አሳላፈፊዎቹ የሉም፤ ሰርግኞቹ ተደብቀዋል፡፡ ኢትጵያዉነት በእሳት ብዛት የማይቀልጥ፣ በዘመን እርዝማኔ የማይለወጥ፣ ደከመ ሲሉት የሚበረታ፣ ተሸነፈ ሲሉት የሚረታ፣ ደበዘዘ ሲሉት የሚፈካ፣ እንንካህ ሲሉት የማይነካ ልዩ ሚስጥር ነው፡፡
ሴራ፣ ክፋትና ምቀኝት ሁሉ ከኢትዮጵያዉነት በታች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዉነት የሚለውን ታላቅ ጥበብ እና ፀጋ ለማጥፋት ብዙ ተደርጓል፡፡ ዳሩ ግን ጥፋተኞች ሲጠፉ ኢትዮጵያዉነት ተሻግሯል፡፡ ነገም ይሻገራል፡፡ ኢትዮጵያን፣ ኢትዮጵያዉያንን እና ኢትዮጵያዉነትን የሚያጠፋቸው የሚስጥራቸው ባለቤት እንጂ ሰው አይደለም፡፡ የሚስጥሩ ባለቤትም እንዳትጠፋ ቃልኪዳን ሰጥቷል፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ደባ የሚያስቡ ሁሉ ከሚስጥሩ እጅግ ያነሱ ስለሆኑ በሚስጥሩ ጥበብ ይጠፋሉ፤ ኢትዮጵያ የጭንቅ ዘመን ተሻግራ ማቋን አውልቃለች፡፡
የማይካድራ፣ የመተከል፣ የጉራ ፈርዳ፣ የወለጋና በሌሎች አካባቢዎች ሁሉ በግፍ የፈሰሰው የአማራ ደም ኢትዮጵያን አፅንቶ ጠላቶቹን ንዷል፡፡ ያለ አይዞሽ ባይ ለአዓመታት የፈሰሰው የአማራ እናት እንባ አባሽ ያገኜ ይመስላል፡፡ ከዚህ በኃላ ልጅ ሰጥታ ሀገር ያተረፈች እናት ማቅ እያወለቀች ነጭ መብሩቅ ትለብሳለች፡፡ እንባዎቿን ጠራርጋ ከትከት ብላ ትስቃለች፡፡ ድሮም ኢትዮጵያዉነት ሙቶ መብዛት፣ ደም አፍስሶ ሀገር ማትረፍ፣ አጥንት ከስክሶ ትውልድ ማሻገር ነውና፤ መሳደድና መቅበዝበዝ ያበቃ ይመስላል፡፡
የደደቢቱ የክፋት መምህሮች ዘመን መቀሌ ላይ ተቋጭቷል፣ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት ጠላት ዘመነ ፍጻሜው ላይ ደርሷል፡፡ በእጅ ያለው ሁሉ ርቆት የቀረው እጁን መስጠት ነው፡፡ ከላበለዚያም ባሩድ መጎንጬት፤ ገድሎ የሚኮራ ኢትዮጵያዊ የለም፣ መግደል፣ መስረቅና መዋሸት ለኢትዮጵያዊያን ነውር ቢሆንም በሀገራቸው የመጣውን ገዳይ፣ ዋሾና ሰራቂ ገድለው ከመቃብሩ አፋፍ ላይ ሆነው ይደሰታሉ፡፡
ለሀገራቸው ሲሉ የማይከፍሉት መስዋትዕነት የለም፡፡ ዘር የሚቆጠር፣ ኢትዮጵያዉነትን የሚሸረሽር፣ ወገን ከወገን ጋር የሚያጠራጥር፣ በእናት ሀገሩ ከባዳ ጋር የሚመሰጥር የክፋት መሪ የተከዳው ክዶታል፣ ጀንበር ጠልቆበታል፤ የኢትዮጵያዉያን ግፍ ከዙፋን ወደ ድንጋይ መቀመጫ መልሶታል፡፡
በእስር ቤት የማቀቁ፣ ከቀያቸው የተናቀሉ፣ ጥፍራቸውን የተነቀሉ፣ ብልታቸውን የተሰለቡና የግፍ ፅዋ የተጎነጩ ሁሉ በጨለማው ዘመን አልፈው የብርሃን ዘመን አምጥተዋል፡፡
ማቅ ለብሳ፣ ደም ያለቀሰችው ኢትዮጵያ እንባዋን ጠርጋ ማቋን አውልቃለች፡፡ የክብሯን ልብስ የማልበስ የተተኪዎቹ ፋንታ ነው፡፡ የኢትዮጵያዉያን ጠላት ሀገራቸውን የሚጠላ ነው፡፡ አሁን ከደቡብ እስከ ሰሜን ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ንፍቅ የፈሰሰው የግፍ ደም በምትኩ በአራቱም አቅጣጫ ፍቅር ያፈሳል፣ አንድነት ያወርሳል፣ አሁን ኢትዮጵያዉያን በኢትዮጵያዉነት የማይፈርስ የጋራ ቤት ውስጥ በጋራ ይጠለላሉ፡፡ ሰላም እና አንድነት ለኢትዮጵያዉያን ሁሉ ይሁን፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleዘላቂ ሠላም፣ ፍትኅ፣ እኩልነትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ማስፈን ቀጣይ ሥራ መሆን እንዳለበት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አስታወቀ።
Next article‹‹ታሪክ የደገሙ የአባቶቻቸው ልጆች››