
ዘላቂ ሠላም፣ ፍትኅ፣ እኩልነትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ማስፈን ቀጣይ ሥራ መሆን እንዳለበት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አስታወቀ።
ባሕር ዳር: ኅዳር 20/2013 (አብመድ)ንቅናቄው የትህነግ ጁንታ ቡድን መደምሰሱን አስመልክቶ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፏል፡፡ በታሪክ ክፍተት እንደዋዛ ለመንበረ ስልጣን የበቃው የትህነግ ስብስብ እድሜውን ሙሉ የጥላቻና ጥፋት ስምሪት በማድረግ ምድቡና ዝርዝሩ የማያልቅ በደል ሲፈፅም መቆየቱን አብን ጠቅሷል።
ንቅናቄው በፌስ ቡክ ገጹ እንደገለጸው ትህነግ የጥላቻና የግፍ ስርአቱን ዳግም ለመጫን ራሱ በከፈተው ጦርነት በጀግናው የሀገር መከላክያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ቅጣቱን ተቀብሎ ታሪክ ሆኖል፡፡ ቀጣይ ትህነግ የተከላቸውን የጥላቻ ትርክት፣ ሕገ-መንግስትና መዋቅሮችን በማፈራረስ ዘላቂ ሰላም፣ ፍትሕ፣ እኩልነትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ማስፈን ይሆናል።
የትሕነግ መደምሰስ ለሀገር በተለይም ከውልደት ጀምሮ በጠላትነት ለፈረጀውና የትየለሌ ግፍ ሲፈፅምበት ለቆየው ለአማራ ሕዝብ እንዲሁም ለትግራይ ሕዝብ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ አብን ገልጿል፡፡
“ለዚህ ድል መረጋገጥ መላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዉያን፣ ሀገር ወዳድ የፖለቲካ በጎ ጥምረቶች ሁሉ ላበረከታችሁት አስተዋፅኦ ልትመሰገኑ ይገባል። በተለይ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ መስዋእትነት ከፍላችሁ ለዚህ ቀን ስላበቃችሁን ክብርና ምስጋና ይገባችኋል።” ብሏል አብን፡፡
የትህነግን የግፍና በደል ማሽን ዘዋሪዎች በፍትኅ አደባባይ የማዋሉ ቀጣይ ሥራ የዚህ ድል ወሳኝ ምዕራፍ መቋጫ እንደሚሆንም ንቅናቄው አስታውቋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ