
“ለዘመቻ ጥሪ ሲደረግ የዓመት ረፍት ላይ ነበርኩ፤ ለግዳጅ የተነሳሁበት ቀን ደግሞ የእህቴ ሰርግ ነበር፤ ጥሪ ሲቀርብ ለሰርግና ለረፍት የሚታሰብበት ጊዜ አልነበረም” ሲስተር በላይነሽ ዋቤ
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 19/2013 ዓ.ም (አብመድ) ሰው ስትሆን መለኪያህ ሰውነት ነው፡፡ እርዳታ በሚያስፈልግበት ሁሉ ትገኛለህ፡፡ ሰውነትህን በጭንቅ ቀን ፈትነህ ስታረጋግጥ እርካታ አለው፡፡ ወገንህን ሊያጠቃ የመጣ ቡድን ጉዳት ሲደርስበት ተንከባክህ መሸኜት ምን አይነት ሰውነት ይሆን? “ጠላትህ ገንዘብህን ሲቀማህ ተሸክመህ ተራራውን አውጣና ሸኜው” እንዳለ መጻሕፍ ሊወጋ የመጣን ሁሉ አክሞ መላክ ምንኛ መታደል ይሆን?
ትዕቢት የወጠረው የትህነግ ቡድን ታላቋን ሀገር ክዶ፣ አለኝታውን ገፍቶ፣ የሀገሪቱን መኩሪያና መከታ ተዳፈረ፣ በጭካኔ ጨፈጨፈ፣ ያ ሳይበቀው በአማራ ሕዝብ ላይም በሌሊት ጥቃት ሰነዘረ፣ ዳሩ ደርሶ አይነካም እንጂ ሲነኩት የሚያርበደብድ ጀግና ነበርና ትህነግን በጫረችው እሳት ያቃጥላት ጀመር፡፡ የአማራ ክልል መንግስት ትህነግ ጥቃት ሰንዝራ የህግ ማስከበሩ በተጀመረ በጥቂት ቀናት ልዩነት የጤና ባለሙያዎችን ወደ ግንባር ልኳል፡፡ ወደ ግንባር የተላኩት የጤና ባለሙያዎችም ለሳምንታት ግዳጃቸውን ተወጥተው ወደ መደበኛ ሥራቸው ተመልሰዋል፡፡ እነርሱን ተክቶ ወደሥፍራው ሌላ ዘማች ሄዷል፡፡
ወታደር ጀግና ነው ጠላቱን ይመክታል፣ አልሞ ተኩሶ ወገኑን ነጻ ያወጣል፡፡ ጦርነት ሲመጣ ተዋጊ ወታደር ብቻ አይደለም የሚያስፈልገው፣ በጦርነቱ የሚዋደቁ ጀግኖችን ደም የሚያብስ፣ ነብስ የሚያተርፍ ሀኪምም ያስፈልጋል፡፡ በዚህ አይነት ወቅት ላይ መገኘት ሰውነትንና ሙያን ይፈትናል፤ ጀግንነትንም ይጠይቃል፡፡ በዚህ ተልዕኮ ሙያዊ አበርክቷቸውን ለመወጣት ወደ ግንባር አቅንተው ከተመለሱ የመጀመሪያው ዙር ዘማች የህክምና ቡድን አባል ከሲስተር በላይነሽ ዋቤ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡
“ለዘመቻ ጥሪ ሲደረግልኝ የዓመት ረፍት ላይ ነበርኩ፡፡ ለግዳጅ የተነሳሁበት ቀን ደግሞ የእህቴ ሰርግ ነበር፡፡ ጥሪ ሲቀርብልኝ ለሰርግና ለረፍት የሚታሰብበት ጊዜ አልነበረም” ያለችው ሲስተር በላይነሽ የእህቷን ደስታ ማዬት ሳይሆን ሀኪም አጥታ የምታሸልብ ነብስ ነበር የጠራቻት፡፡ አላቅማማችም ወደ ዘመቻ ለመሄድ ተዘጋጄች፡፡ ሄደችም፡፡ “ውሳኔዬ ልክ ነበር፣ በአብርሃጅራ ሆስፒታል ስንደርስ ሰው በየወለሉና በየጥጋጥጉ ወድቆ ነበር፣ በጉዟችን የያዝነውን እቃ እንኳን አላስቀመጥንም፣ ወደሥራ ነው የገባነው፡፡ በሆስፒታሉ የነበሩ ባለሙያዎቹ ሁሉንም ማስተናገድ አልቻሉም ነበር፤ እኛ ደርሰን ብዙ ነብሶችን መታደግ ችለናል፣ ደስታውን እንድታይለት የሚፈልግ ቤተሰብ በጦርነት መካከል ስትሄድ ያዝናል፣ አንተም ታዝናለህ፣ ነገር ግን ቤተሰብ ከሀገር አይበልጥም፣ ሀገሬን አስቀድሜ ነው የሄድኩት፣ ሀገር ከሌለ ቤተሰብ አይኖርም፣ ደስታም ማዬት አትችልም፣ ሀገር ሲኖር ነው ሁሉም የሚያምረው፣ እኔ ሄጄ በሙያዬ አንድ ሰው ሁለት ሰው ሕይወት ብታደግ ለእኔ ከዚያ በላይ ደስታ የለም፣ ደስታው ያ ነው የሚበልጥብኝ ” ነው ያለችው፡፡
ሁኔታው ችግር ከበደን ብሎ መሸሽ እንደማያስፈልግ የተረዳችበት፣ ይሄኛው ወገን የዚህ ነው፣ ያንኛው ደግሞ የዚያ ነው ብሎ የማይለይበት፣ የሙያ ስነምግባር እንዴት መተግባር እንዳለበት የተረዳችበት መሆኑንም ተናግራለች፡፡ “በዚያ ግዳጅ በማገልገሌ ደስ ብሎኛል፣ ምክንያቱም ከሁለቱም ወገን የሚገኜውን ተጎጂ በእኩል መንገድ ስናገለግል ስለነበር፣ ባለሙያ መሆን ምን ያክል እውነት እንደሆነ መረዳት ችያለሁ” ነው ያለችው፡፡
የትህነግ ቡድን ቁስለኞች ” ሲያዩን ይፈራሉ፣ እንቅስቃሴያችንን ሁሉ ይከታተላሉ፣ መድኃኒት ስንሰጣቸው ይሄ ምንድን ነው ይሉናል፣ እኛ ባለሙያ ስለሆን የሚጠይቁንን ሁሉ እንመልሳለን፣ ቁስላቸውን ስናሽግላቸውና ስናፀዳላቸው ይጠይቁናል፣ ቁስላችሁ ካልተፀዳ ለሌላ ችግር ትጋለጣላችሁ እያልን ስንከባከባቸው አመለካከታቸው ይቀየራል፤ በምናሳያቸው ፍቅር ይደሰታሉ፡፡ ከዳኑ በኃላ እኛ እኮ እንደዚህ አይመስለንም ነበር ይሉናል፣ መጀመሪያ ላይ የነበራቸው ፍራቻ ተወግዶ እውነታውን ሲያውቁ የሚሰጡን ምላሽ ያስደስተኛል” ነው ያለችው ሲስተር በላይነሽ፡፡
“የትህነግ ቡድን ቁስለኞች በትግርኛ ሲያወሩን መረዳት አልችል ብለን ተቸግረን ነበር፣ ህክምናውን በምልክት መስጠት ጀመርን፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አማርኛ የሚችል ሰው ፈልገን ህክምና እንሰጥ ነበር ፤ እነርሱ አስበውት የመጡትና እኛ የምናደርግላቸው እርዳታ በጣም ልዩነት ስላለው በደስታ አመስግነውን ይሄዳሉ” ነበር ያለችኝ፡፡
ከአብርሃጅራ ሆስፒታል እስከ ሁመራ ሆስፒታል ድረስ ሲያገለግሉ እንደነበር የተናገረችው ሲስተር በላይነሽ ወደማይካድራ ሲሄዱ የነበረውን ሁነት ስታስታውሰው “ወደሥፍራው ስናቃና ጤና ጣብያው ተዘግቶ ነበር፣ በእኛ አማካኝነት ተከፈተ፣ ግድያውን ለማምለጥ ሲሄዱ በየጫካው የወደቁ ሰዎች ነበሩ፣ እነርሱን እያሰስን፣ እርዳታ እየሰጠን ወደ አብርሃጅራ ሆስፒታል ሪፈር እየላክን፣ በብዙ መስዋዕትነት ትልቅ ሥራ ሰርተናል፣ ነብስም ታድገናል” ነው ያለችው፡፡
ያ ጊዜ ለሲስተር በላይነሽ የሰውን ልዩ ልዩ ባሕሪ ያሳያት ነበር፡፡ ሁመራ ሆስፒታል ሲደርሱ አብዛኛው ቁስለኛ የትህነግ ልዩ ኃይሎች ነበሩ ፡፡ ሆስፒታሉን አስቀድመው ዘግተውት ሄደው 22 የሚደርሱ ሰዎች መሞታቸው ከአሁን ቀደም መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ልብ ይበሉ ሆስፒታል ዘግተው የጠፉትም፣ ሆስፒታል ከፍተው የገቡትም ሁለቱም ተመሳሳይ ቃለ መሃላ የፈፀሙ፣ ተመሳሳይ የሙያ ስነምግባር የሚገዛቸው ናቸው፡፡ ሰዎችም ናቸው፡፡ ግን አምሳለ ሰውና ሰው መሆን የሚለዬው በተግባር ነው፡፡ ከሙያ ስነምግባሩ በላይ ሰውነት ይፈተናል፡፡ እነ ሲስተር በላይነሽ ሁመራ ከመድረሳቸው በፊት የተፈፀመው ግፍ ቃል ኪዳናቸውን አላስረሳቸውም፣ የማይካድራው ዘር የለዬ ጭፍጨፋ ስነ ምግባራቸውን አላስጣሳቸውም፣ በሆስፒታሉ የተገኙትንና የሚመጡትን ብዙ ቁጥር ያላቸው የትህነግ ቡድን ቁስለኞችን አክመው ከሞት አትርፈዋል፡፡
” የተጎዳውን ማህበረሰብ ስታይ መቋቋም የማትችለው ሀዘን ነው የሚሰማህ፤ ያንን ጉዳት ያደረሰ ሰው እጅህ ላይ ሲወድቅ ያንን አታስበውም፣ የጉዳቱን መጠን ነው የምታዬው፣ መርዳት ያለብህን ብቻ ነው የምታስበው፣ እንደዚህ አድርጎ ነበር የሚለው ጭንቅላትህ ውስጥ አይመጣም፣ ማሰብም አትችልም፣ በህክምና ቦታ ስትሆን ደስ የሚያሰኜው ነገር ይሄ ነው” ብላለች ሲስተር በላይነሽ፡፡
ሲስተር በላይነሽ በነበራት ቆይታ ምን አይነት ምስል እንደተፈጠረባት ስትናገር ‹‹ ለምን ሰው አድርገህ ፈጠርከኝ ሁሉ ብያለሁ፣ ሬሳ በጥጥና በሰሊጥ ውስጥ ወድቆ ስታይ፣ የተጎዳ ሰው ጣረ ሞት ላይ ሆኖ ስታይ፣ ልትቋቋመው የማትችለው አይነት ስሜት ይሰማሃል፣ ስነ ልቦና ላይ የሚፈጥረው ጠባሳ አለ፤ ወደ መደበኛ ሕይወት ለመመለስ ጊዜ ይወስዳል›› ነበር ያለችው፡፡ ልብ ይበሉ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች የልብ ስብራት መች ይመለስ ይሆን? እኒያ የማይካድራ እናቶች ጩኸት እስከመች ይቀጥል ይሆን ? ወንድ ልጅሽን ስጭን ተብላ የአብራኳ ክፋይ ፊት ለፊቷ ላይ አንገቱ ሲቀላ ያዬችው እናት ልቦናዋ መች ነው የሚጠገነው? ፈጣሪ ይወቅ፤ ፍርዱንም እርሱ ይስጥ፡፡
ሲስተር በላይነሽ ከሙያዋ ባሻገር የታዘበችውስ “የአካባቢው ተወላጆች በነጻነት ሲኖሩ አልነበረም፣ አሁን ላይ ግን ነፃ በመውጣታቸው ደስተኞች ናቸው፡፡ እኛ ብንሞት ሌላው ሕዝብ በነጻነት ይኖራል ይሉን ነበር” ነው ያለችው፡፡
የትህነግ ግፍ ሞልቶ ፈስሷል፣ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ደጅም ደርሷል፣ አሁን ግን የግፉ ማክተሚያ ላይ ደርሷል፤ ከትህነግ ፍጻሜ በኋላ የጅምላ መቃበር ይጠፋል፣ የጨለማ እስር ቤቶች ይከፈታሉ፣ ወገን ወገኑን በጥርጣሬ ማየት ይቆማል፣ የደም ጎርፍ ይደርቃል፣ ይህ የኢትዮጵያዊያን ተስፋ ነው፡፡ ደግሞም ተስፋቸው ሩቅ አይሆንም፡፡
በታርቆ ክንዴ