በማይካድራ ተጨማሪ የጅምላ መቃብሮች ተገኙ።

778

በማይካድራ ተጨማሪ የጅምላ መቃብሮች ተገኙ።

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 18/2013 ዓ.ም (አብመድ) ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም በንጹኃን የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ዘርን መሠረት ያደረገ ጥቃት በማይካድራ ከተማ መፈፀሙ ይታወቃል። ይህን አስነዋሪ ተግባር የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በቦታው በመገኘት ባደረገው ጥናት እና ይፋ ባደረገው መረጃ የሟቾች ቁጥር በትንሹ 600 እንደሆነ ገልጾ ነበር።
ግድያውም ዘርን መሠረት ያደረገና በተለይም የአማራ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ጅምላ ጭፍጨፋ መሆኑን ገልጿል። ይሁን እንጂ የሟቾች ቁጥር በትንሹ 600 ነው ተብሎ የተገለጸው በማይካድራ ከተማ በየቤቱ ህይወታቸው አልፎ የተገኙ እና በቤተክርስቲያን ውስጥ የተቀበሩትን ብቻ መሠረት ያደረገ ነው።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጥናት አድርጎ ከተመለሠ በኃላ ከማይካድራ ከተማ ወጣ ባሉ የገጠር አካባቢዎች በርካታ የጅምላ መቃብሮች መገኘታቸውን የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ጋዜጠኞች በቦታው በመገኘት አረጋግጠዋል።
በአንድ ቦታ 18 ሰው በጉድጓድ ውስጥ በጅምላ የተጣሉ ሲሆን በሌላ የገጠር አካባቢ ደግሞ 57 ሰዎች በጎርፍ ማፋሰሻ ቦይ ውስጥ በጅምላ ተገድለው እና ተጥለው ተገኝተዋል።
በዛሬው ዕለትም በማይካድራ ሌላ የገጠር ቀበሌ ውስጥ 17 ሰዎች በጅምላ ተገድለው በጉድጓድ ውስጥ ተጥለው ተገኝተዋል። አሁንም ሴንትራል፣ ደሮ እርባታ፣ በረኸት በሚባሉ አካባቢዎች ላይ አሠሳ እየተደረገ እንደሚገኝ እና ቁጥሩ እንደሚጨምር የማይካድራ ነዋሪዎች ገልጸውልናል።
በዚህ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተሳታፊ ናቸው የሚባሉት ተጠርጣሪዎች በብዛት ሱዳን ሐሻባ በሚባል የስደተኞች መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ ይነገራል።
ከዚህ በተጨማሪ በማይካድራ የዘር ማጥፋት ወንጀል ላይ ተሳታፊ ናቸው በሚል ተጠርጥረው ከተያዙት 60 ግለሠቦች ውስጥ 17ቱ በቀጥታ የወንጀሉ ተሳታፊ መሆናቸውን የማይካድራ ከተማ ጊዜያዊ አስተዳደር ገልጾልናል።
ትህነግ በወልቃይትና አካባቢው ተወላጆች ላይ በአስር ሽህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ገድሏል፤ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ሰዎችን ደግሞ ከአካባቢያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል፡፡
ዘጋቢ፡- ሱራፌል ስንታየሁ – ከማይካድራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“የልዩ ኃይሉና የሚሊሻ ተጋድሎ ከዛታ ተራሮች ስር ”
Next article“ለዘመቻ ጥሪ ሲደረግ የዓመት ረፍት ላይ ነበርኩ፤ ለግዳጅ የተነሳሁበት ቀን ደግሞ የእህቴ ሰርግ ነበር፤ ጥሪ ሲቀርብ ለሰርግና ለረፍት የሚታሰብበት ጊዜ አልነበረም” ሲስተር በላይነሽ ዋቤ