“የአምባገነን መሪዎች ባህሪና እጣ ፋንታ”

727

“የአምባገነን መሪዎች ባህሪና እጣ ፋንታ”

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 17/2013 ዓ.ም (አብመድ) አምባገነን መሪዎች አንድ የሚያደርጓቸው ብዙ ባህሪያት አላቸው። ከእነዚህ ባህሪዎቻቸው መካከል ደግሞ የሀገርን ሀብት መበዝበዝ አንዱ ነው። የህዝባቸውን ኑሮ ለማሻሻል ከመጣር ይልቅ የሀገርን ሀብት በመዝረፍ ለግላቸው ያከማቻሉ።
እ.አ.አ በ2004 ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ‹‹የምንጊዜም ሙሰኞች›› ብሎ ከፈረጃቸው አምባገነኖች መካከል የኢንዶንዥያው አምባገነን መሪ የነበረው መሐመድ ሱሃርቶ እስከ 30 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሀገርና የህዝብ ገንዘብ ዘርፏል፤ የፊሊፒንሱ ፈርዲናንድ ማርቆስ እስከ 10 ቢሊዮን ዶላር በመዝረፍም ስሙ ይጠቀሳል፡፡ የቀድሞው የዛየር የአሁኑዋ የኮንጎ መሪ የነበረው ሞቡቱ ሴሴሴኮ ደግሞ ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከደሃ ህዝብና ሀገር በመዝረፍ ለግል ጥቅሙ አውሏል፡፡
ሁለተኛው ባህሪያቸው ደግሞ ህዝብን መጨፍጨፋቸው ነው፡፡ በዚህም ስማቸው በዓለም ላይ በጥቁር መዝገብ ከሰፈሩ አምባገነኖች መካከል የቻይናው ማኦ ዜዶንግ፣ የቀድሞው የሶቭየት ህብረት መሪ ጆሴፍ ስታሊን፣ የጀርመኑ አዶልፍ ሂትለር፣ የቤልጀሙ ንጉስ ሊኦፓልድ ዳግማዊ እና የጃፓኑ ሂዶኪ ቶጆ የራሳቸውን ዜጎችና በመጥፎ የፈረጇቸውን ህዝቦች ጭምር በበሽታ፣ በርሃብ፣ በመርዝ፣ በጥይት እና በተለያዩ ዘዴዎች በመግደል የክፋት ጥጋቸውን አሳይተዋል። እነዚህ መሪዎች ‹‹እጅግ የከፉ አረመኔዎች›› ተብለው ስማቸው ይነሳል፡፡
አፍሪካም እንደሌሎች ክፍለ ዓለማት በርካታ አምባገነን መሪዎችን አስተናግዳለች። እነዚህ አምባገነን መሪዎች ከሌሎች ክፍለ ዓለማት አምባገነኖች የሚለዩት የቀድሞዎችን መሪዎች ውድቀት እና ውርደት አይተው የማይታረሙ፣ ካዩትና ከሰሙት ስህተት የማይማሩ መሆናቸው ነው። በዚህም ምክንያት የበለጸጉ ሀገሮች በገፍ ባመረቱት ጠመንጃ ምስኪኗ አፍሪካ ቁም ስቀሏን አይታለች፡፡
ከአፍሪካ አምባገነን መሪዎች የኡጋንዳው መሪ የነበረው ኢዲአሚን ዳዳ ይጠቀሳል። ኢዲአሚን ዳዳ የፕሬዚዳንት ሚልተን ኦቦቴን ሥርዓት በመፈንቅለ መንግስት አስወግዶ ስልጣን ከያዘ በኋላ በገዛ ህዝቡ ላይ ጭፍጨፋ አካሂዶ ‹‹የኡጋንዳ አራጅ›› የሚል ቅፅል ስም ተሠጥቶታል። በርካታ የኡጋንዳ ዜጎችም ወደ ታንዛኒያ በመሰደድ ስርዓቱን መቃወም ጀመሩ። የወቅቱ የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት የነበረው ጁሌየስ ኔሬሬም የኡጋንዳ አማጺያንን በማስተባበር ከስልጣን እንዲወገድ ተደረገ።
በቅርቡ ከስልጣን የወረደው የጎረቤት ሀገር ሱዳን መሪ ኡመር ሐሰን አልበሽር እ.አ.አ በ1989 የጠቅላይ ሚኒስትር ሳዲቅ አልማህዲን መንግስት በመፈንቅለ መንግስት አስወግዶ ስልጣን ከያዘ በኋላ በቆዳ ስፋቷ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነችውን ሀገር እንደሚያረጋጋት ቃል ገብቶ ነበር።
ይሁን እንጂ የገባውን ቃል በማጠፍ ሱዳን በሁለት እንድትከፈል አድርጓል። ከዚህ በተጨማሪም ዳርፉር ላይ ‹‹ጃንጃዊድ›› የተባሉ ሚሊሻዎችን በማሰማራት በሰብአዊ ፍጡር ላይ በፈጸመው ወንጀል ዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የእስር ትዕዛዝ አውጥቶበት እንደነበር ይታወሳል። በመጨረሻም እ.አ.አ በ2019 በወታደራዊ ቡድን ከስልጣን ተወግዷል፡፡
የላይቤሪያው አምባገነን መሪ ሳሙኤል ካንዮን ዶ በግንባር ቀደምነት ከሚጠቀሱት አረመኔ መሪዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ይነገራል። ይህ ሰው ስልጣን ከወጣ ጀምሮ ሁሉን የመንግስት ስልጣን በጎሳው አባላት እንዲያዝ በማድረግ በርካታ የሀገሪቱን ዜጎች ጨፍጭፏል። በተለይ ደግሞ የቀድሞ ባለስልጣናት በአትላንቲክ ውቅያኖስ ዳርቻዎች እርቃናቸውን ታስረው በጥይት እንዲጨፈጨፉ አድርጓል። በመጨረሻም አገዛዙ ያንገሸገሻቸው ላይቤሪያውያን ባካሄዱት አስከፊ ጦርነት በአማጺያኑ ቁጥጥር ስር ውሎ ሊገደል ችሏል።
ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣም የቀዳማዊ ኃይለስላሴ የዘውድ አገዛዝ በወታደራዊ መንግስት ከተወገደ በኋላ በርካታ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በየስርቻው ተመሰረቱ፡፡ ስርዓቱን በኃይል ለመገርሰስም እንቅስቃሴ ጀመሩ፡፡
ደርግን በኃይል ለማስወገድ ነፍጥ አንግበው ወደ ጫካ ከገቡት ኃይሎች መካከል ደግሞ ሕወሃት አንዱ ነው፡፡ ትግሉ ጨቋኙን የደርግ መንግስት በማስወገድ ሰላም፣ ዴሞክራሲ እና የብሄር ብሄረሰቦችን እኩልነት ለማስፈን እንደሆነ ብዙ የይስሙላ ፕሮፖጋንዳዎችን ህወሀት ነዛ፡፡ በዚህም በርካታ ወጣቶች ህይወታቸውን ገብረዋል፤ ለአካል ጉዳትም ተዳርገዋል፡፡ ይሁን እንጅ የተዘመረለት ሰላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲና እኩልነት ኮስምኖ በምትኩ በሀገሪቱ ተንቀሳቅሶ ለመስራት ፈታኝ የሆነበት እና በርካታ ሃብት የተዘረፈባት ሀገርም ሆነች – ኢትዮጵያ፡፡ በዚህም በርካታ ዜጎች በጉራ ፈርዳ፣ በበደኖ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ዜጎች በግፍ ተገደሉ፡፡ በምርጫ 1997ም በርካታ ዜጎች ህይወታቸውን እንዲያጡ አድርጓል፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማሪያም ‹‹የክህደት ቁልቁለት›› በሚል ባሳተሙት መጽሃፍ ላይ ይህንን የህወሀት የክፋት ጥግ ሲገልጹ ‹‹የህወሀት መሠረትና መነሻ ጥላቻ ነው፤ ጥላቻ ብዙውን ጊዜ ከፍራቻ ጋር የተቆራኘ ነው፤ ሁለቱም ስሜቶች ልብንም፣ አዕምሮንም፣ መንፈስንም የሚጋርዱና የሰውን ልጅ ዝቅ የሚያደርጉ ናቸው፤ ጥላቻን መሠረት አድርጎ የተነሳ ቡድን ጥሩ ነገር መሥራት አይችልም፤ ፍርሃት እና ጥላቻ የተቆራኙበት ቡድን ወይም ግለሰብ ከቅርብ ሰዎች ጋር ከመተባበር ይልቅ ባዕድ ሰዎችን ያቀርባል›› ብለዋል።
ጥላቻ ባህሪው የሆነው ቡድንም ‹‹ለውጡን›› በወቃወምም መቀሌ ላይ መሸገ፡፡ ከፌደራሉ መንግስት ጋር እሰጣ ገባ ከመግባት ባለፈም መልሶ ስልጣን ለመያዝ የሚያስችለውን ሃይል መገንባት ላይ ተጠመደ፡፡ ህገ መንግስቱን በመጣስም የስልጣን ጥሙን ለማረካት ምርጫ አካሄደ፡፡
በመጨረሻም የአፍሪካ ኩራት በሆነው የሰሜን ዕዝ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ፈጸመ፡፡ ይህንን ተከትሎም የፌደራል መንግስት ህግን ለማስከበር እርምጃ እየወሰደ ባለበት ወቅት በሁመራ ማይካድራ በንጹሃን ዜጎች ላይ የግፍ ጨፍጨፋ አደረገ፡፡
ታዲያ የህወሃት የመጨረሻ እጣፋንታ ምን ይሆን?
የክህደት ቁልቁለት እና የገሃነብ ዳንኪረኞች መጽሃፍትን እንዲሁም ቢቢሲን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል፡፡
በዳግማዊ ተሰራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበጋምቤላ ክልል በጁንታው ታቅዶ የነበረ የጥፋት ሴራ መክሸፉ ተገለጸ፡፡
Next articleየኢትዮጵያ ቅርሶች አስመላሽ ብሔራዊ ኮሚቴ ተመሰረተ፡፡