
በጋምቤላ ክልል በጁንታው ታቅዶ የነበረ የጥፋት ሴራ መክሸፉ ተገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 17/2013 ዓ.ም (አብመድ) በጋምቤላ ክልል በህወሃት ጁንታ ታቅዶ የነበረ የጥፋት ሴራ በህዝቡና በጸጥታ ኃይሉ የተቀናጀ ጥረት ማክሸፍ መቻሉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስታወቁ።
ጁንታው በክልሉ ዘርግቶት የነበረውን የጥፋት መረብ ሙሉ ለሙሉ ለመበጣጠስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳደሩ እንዳሉት በጁንታው ታቅዶ የነበረው የጥፋት ሴራ መረጃ ቀድሞ በመድረሱ በጸጥታ ኃይል አስፈላጊው ጥናት ተካሄዶ ሴራውን ማክሸፍ ተችሏል።
“በዚህም ችግር ሊፈጥሩ የነበሩ አብዛኛዎቹ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል“ ብለዋል። ቀሪዎቹን ለመያዝም በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ርዕሰ መስተዳደሩ ገልጸዋል።
የህወሃት ጁንታ ህዋስ በክልሉ በብዛት እንደነበረ ያስታወሱት አቶ ኡሞድ፤ “ክልሉ የቡድኑ የጥቃት ኢላማ ይሆናል የሚል ስጋት በመኖሩ ሰፊ የመከላከል ስራ ተሰርቷል” ብለዋል።
አካባቢውን የብጥብጥ ቀጠና እንዲሆን ታቅዶ የነበረው የጥፋት ሴራ በህዝብና በጸጥታው ሃይሉ የተቀናጀ ጥረት ማክሸፍ መቻሉን አስታውቀዋል።
ክልሉን ከደቡብ ሱዳን ጋር በሚያገናኙ የመግቢያና የመውጫ በሮች የጥፋት ቡድኑ አባላት ወደ ደቡብ ሱዳን ለመኮብለል እየሞከሩ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
ድንበር አቋርጠው ለመውጣት የሞከሩ የቡድኑ አባላት መያዛቸውን ጠቁመው፤ “የጥፋት ቡድኑን መንገድ በመምራት ለማሸሽ የሞከሩ ሶስት ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል” ነው ያሉት።
በአካባቢው አስፈላጊው የጸጥታ ኃይል ተመድቦ የተጠናከረ ክትትልና ጥበቃ እየተደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ የጁንታውን ሴራ እስከ መጨረሻው ለማምከን በተጀመረው ህግን የማስከበር ስራ የክልሉ ህዝብ ሁለንተናዊ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ርዕሰ መስተዳድሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በክልሉ ከህወሓት ቡድንና ኦነግ ሸኔ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ 65 ግለሰቦች የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥጥር ስር ማዋሉ ይታወሳል።