
የጋሸና-ላልይበላ-ሰቆጣ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ቀሪ ስራዎች በተያዘው በጀት ዓመት እንዲጠናቀቁ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 17/2013 ዓ.ም (አብመድ) የጋሸና-ላልይበላ-ሰቆጣ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ 204 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመት ይሸፍናል፡፡
የጋሸና-ላልይበላ-ሰቆጣ መንገድ አካል የሆነው የጋሸና-ቢልባላ አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ከአጠቃላይ 105 ኪ.ሜ ርዝመት ውስጥ 87 በመቶ ደርሷል፤ በተያዘው ዓመት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል ብሏል ባለስልጣኑ ።
የጋሸና-ቢልባላ አስፋልት ኮንክሪት መንገድ በአሁኑ ወቅት 78 ኪሎ ሜትሩ የአስፋልት ንጣፍ ስራው እንደተከናወነ ባለስልጣኑ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጹ አስፍሯል።
ፕሮጀክቱን በ1 ነጥብ 87 ቢሊዮን ብር በሆነ ወጪ በመገንባት ላይ የሚገኘው አለማቀፉ ቻይና ሬል ዌይ ኢንጅነሪንግ ቁጥር 3 የስራ ተቋራጭ ነው።
የማማከርና የቁጥጥር ስራውን ኢንጂነር ዘውዴ እና ዋይ ኤል ኤስ ኢንጂነሪንግ አማካሪ ድርጅቶች በጣምራ እያከናወኑት ይገኛል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘም 99 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የሚዘልቀው የመንገድ የፕሮጀክቱ ቀጣይ ክፍል የሆነው የቢልባላ-ሰቆጣ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ከአጠቃላይ የግንባታ ስራ ውስጥ 80 በመቶ ደርሷል።
ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታውን በማካሄድ ላይ የሚገኘው ቻይና ፈርስት ሃይ ዌይ ኢንጂነሪንግ የተባለ የቻይና ዓለም አቀፍ የሥራ ተቋራጭ ድርጅት ነው፡፡
ሃገር በቀሉ ቤስት ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ የቁጥጥርና የማማከር ሥራውን እያካሄደው ይገኛል።
የጋሸና-ላልይበላ-ሰቆጣ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ቀሪዎቹን ስራዎች በተያዘው በጀት ዓመት በተገቢው የጥራት ደረጃና ፍጥነት እንዲጠናቀቁ ለማስቻል እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡
የመንገድ ፕሮጀክቱ ካለው ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጠቀሜታ አንጻር እንዲሁም በቀጣይ መንግዱ ሊያስተናግድ ከሚችለው ብዛት ያለው ተሸከርካሪ አንጻር በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ እየተገነባ ያለ መንገድ መሆኑ ተጠቅሷል።
መንገዱ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ በቂ የሆነ የመንገድ መሰረተ ልማት ያልነበረውን የአካባቢውን ሕብረተሰብ የዘመናዊ ትራንስፖርት ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል ነው የተባለው።
አርሶ አደሮች ምርታቸውን በቀላሉና በተቀላጠፈ ሁኔታ ወደ ተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች ለማመላለስ እንደሚያስችል ተመልክቷል፡፡
የመንገዱ መገንባት ለሀገር ውስጥና ለውጪ ጎብኝዎች በዓለም የቅርስ መዝገብ ላይ ተመዝግቦ ያለውን የላሊበላን እና ሌሎች በአካባቢው የሚገኙ ጥንታዊ እና ታሪካዊ ቦታዎችን ለመጎብኘት ሁለተናዊ ፋይዳው የጎላ ነው ተብሏል፡፡
የጋሸና-ላልይበላ-ሰቆጣ የመንገድ ፕሮጀክት ወጪ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግስት ተሸፍኖ እየተሰራ ይገኛል፡፡


