ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በፓሪስ ተገናኝተው መክረዋል።

271
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በፓሪስ ተገናኝተው መክረዋል።
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 17/2013 ዓ.ም (አብመድ) የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በአውሮፓ ሃገሮች የዲፕሎማሲ ተልዕኮ ጉዟቸው ዛሬ በፈረንሳይ ቀጥሏል።
በኤሊዜ ቤተመንግሥት የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የተላከውን መልዕክት ለፕሬዝዳንት ማክሮን አድርሰዋል።
በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ በሚፈለገው ጥራት እና ፍጥነት ለማስቀጠል ከሁለት ዓመታት በላይ መንግሥት አስፈላጊውን ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንም አስረድተዋል።
እንደ አቶ ደመቀ ገለፃ የወንበዴው የህውሃት ቡድን በህዝቡ እና በመንግሥት ላይ ተደጋጋሚ ጥፋቶችን ሲፈፅም እንደነበር አስታውሰዋል።
በመንግሥት በኩል ችግሩን በሰላም እና በውይይት ለመፍታት ተደጋጋሚ ጥረቶች ቢደረጉም፤ በአንፃሩ የወንበዴው ቡድን እኩይ ድርጊቶችን መፈፀሙን አጠናክሮ እንደገፋበት ተናግረዋል።
በሂደት አስገዳጅ እና አሳዛኝ ድርጊቶች መፈጠራቸውን ተከትሎ መንግስት ህግ የማስከበር እርምጃ እየወሰደ የመጨረሻው ዘመቻ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ገልፀዋል።
ፕሬዚዳንት ማክሮን በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት የውስጥ ጉዳዩን በራሱ ለመፍታት የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን በመጠቆም፤ ህግ በማስከበር እርምጃ ሂደት የንፁህ ዜጎች ደህንነት ተገቢውን ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል።
በዘመቻው የአስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ መንግሥት የጀመረው ጥረት የሚበረታታ በመሆኑ፤ በቀጣይ ለተቀናጀ ሰብዓዊ እርዳታ አስቻይ መደላድሎች እንዲጠናከሩ ጠይቀዋል።
በመጨረሻም የኢትዮ-ፈረንሳይ ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች ከደረሱበት የትብብር ምዕራፍ በተሻለ ደረጃ ለማጠናከር መንግስታቸው ዝግጁ መሆኑን ፕሬዚዳንት ማክሮን ማረጋገጣቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይፋዊ የማህበራዊ ትስስር የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
Previous articleየመጨረሻው የዘመቻው ምዕራፍ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አስታወቁ፡፡
Next articleየጋሸና-ላልይበላ-ሰቆጣ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ቀሪ ስራዎች በተያዘው በጀት ዓመት እንዲጠናቀቁ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡