የመጨረሻው የዘመቻው ምዕራፍ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አስታወቁ፡፡

233
የመጨረሻው የዘመቻው ምዕራፍ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አስታወቁ፡፡
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 17/2013 ዓ.ም (አብመድ) ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህግ የማስከበር የህልውና ዘመቻ አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው የሚከተለውን መልዕክት አስፍረዋል፡፡
የተሰጠው የ72 ሰዓት ጊዜ ተጠናቅቋል፤ ሕግ የማስከበር ዘመቻችን የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡ በተሰጠው የ72 ሰዓት ጊዜ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ አባላት እጃቸውን ለመከላከያ ሠራዊት ሰጥተዋል፡፡ ብዙ የትግራይ ወጣቶችም የሕወሐትን እኩይ ዓላማ ተረድተው እጃቸውን ሰብስበዋል፡፡ ይህ በመጨረሻው ሰዓትም ቢሆን የተወሰደ ኃላፊነት የሚሰማው ውሳኔ ኅሊና ካለው ፍጡር የሚጠበቅ ውሳኔ ነው፡፡
መንግሥት 72 ሰዓት ሲሰጥ ዓላማው ሁለት ነበር፡፡ በአንድ በኩል ዋና ፍላጎቱ ሕግ ማስከበር እንጂ ጦርነት አለመሆኑን መግለጽ ነው፡፡ ወንጀለኛው ጁንታ በሰላም እጁን ለመስጠት ከቻለ ዘመቻውን በማጠናቀቅ ሕግን በአነስተኛ ዋጋ ለማስከበር ይቻላል ብሎ ያምናል፡፡ ለዚህም ሲባል ተደጋጋሚ ዕድሎችን ሰጥቶ ነበር፡፡
ሁለተኛው ደግሞ የሕወሐት የጥፋት ዓላማ ዘግይቶም ቢሆን የገባው አንድም ሰው ከተገኘ፣ ያንን ሰው ለማትረፍ እንዲቻል ነው። ለሕወሐት ጁንታ የተከፈተው የመጨረሻው ሰላማዊ በር በጁንታው ዕብሪት ምክንያት ተዘግቷል፡፡ የጥፋታቸውን ዓላማ ተገንዝቦ ለሚመለስ ሰው በተከፈተው በር ግን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ሚሊሻና ልዩ ኃይል አባላት እጃቸውን እየሰጡ ገብተውበታል፡፡
የመከላከያ ሠራዊታችን የመጨረሻውንና ሦስተኛውን የዘመቻውን ምእራፍ እንዲፈጽም ትእዛዝ ተሰጥቷል፡፡ በዚህ ዘመቻችን ለንጹሐን ሰዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እናደርጋለን፤ በሕዝባችን ላብ የተሠራችው የመቀሌ ከተማ የከፋ ጉዳት እንዳያገኛት የሚቻለው ሁሉ ይደረጋል፡፡ ቅርሶች፣ ቤተ እምነቶች፣ የሕዝብ መገልገያዎች፣ የልማት ተቋማትና የሕዝብ መኖሪያዎች የጥቃት ዒላማ እንዳይሆኑ ሁሉም ዓይነት ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡
የመቀሌና የአካባቢው ሕዝባችን ትጥቁን ፈትቶ በቤቱ በመቀመጥና ከወታደራዊ ዒላማዎች በመራቅ፣ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሁሉ እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ በጥቂት የሕወሐት ጁንታ አባላት ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ሕዝቡ የጁንታውን አባላት አሳልፎ በመስጠት የበኩሉን አስተዋጽዖ እንዲያደርግ ጥሪ እናደርጋለን፡፡
የመከላከያ ሠራዊታችን በሰላማዊ ዜጎች፣ በቅርሶች፣ በቤተ እምነቶች፣ በልማት ተቋማትና በንብረቶች ላይ ጉዳት ሳይደርስ ጁንታውን ለሕግ የሚያቀርብበትን ጥንቃቄ የተሞላው የዘመቻ ስልት የነደፈ መሆኑን ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን፡፡
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ኅዳር 17 ቀን 2013 ዓ.ም
Previous articleየወረታ ደረቅ ወደብ ሥራ መጀመር በአስመጪና ላኪዎች ይደርስ የነበረውን እንግልት እየፈታ መሆኑን የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
Next articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በፓሪስ ተገናኝተው መክረዋል።