የወረታ ደረቅ ወደብ ሥራ መጀመር በአስመጪና ላኪዎች ይደርስ የነበረውን እንግልት እየፈታ መሆኑን የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

632
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 17/2013 ዓ.ም (አብመድ) የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው በሦስት ሄክታር ላይ ያረፈው የወረታ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ሥራ በመጀመር የገቢና ወጪ ንግዱን በማሳለጥ ጉልሕ ሚና እተጫወተ ይገኛል፡፡ ከአሁን በፊት በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ አስመጪና ላኪዎች የሚጠቀሙት የኮምቦልቻ ደረቅ ወደብን ብቻ ነበር። የኮምቦልቻ ደረቅ ወደብና ተርሚናል በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ አስመጪና ላኪዎችን ለማስተናገድ በቂ ባለመሆኑ በክልሉ ተጨማሪ አማራጭ እንዲኖር ጥያቄ ሲነሳ ነበር፡፡
የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክ አገልግሎትም አስፈላጊነቱን በመረዳት የወረታ ደረቅ ወደብና ተርሚናልን ገንብቶ ሥራ አስጀምሯል፡፡ የወረታ ደረቅ ወደብ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ለአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ለአስመጪና ላኪዎች እንዲሁም ለክልሉ መንግሥት ከፍተኛ ምጣኔሀብታዊ ጥቅም ይዞ መቅረቡን የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ ተስፋዬ አያሌው ተናግረዋል፡፡ የወጭና የገቢ ንግዱን በከፍተኛ ደረጃ እያሳለጠው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ከውጪ ሀገር የሚገባ ንብረት ሲደርስም ለባለሀብቶች በማሳወቅ በአጭር ጊዜ እንዲረከቡ እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ደረቅ ወደቡ ሥራ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ 3 ሺህ 66 ሙሉ ገቢ፣ ሙሉ ወጪ፣ ባዶ ገቢና ባዶ ወጪ ኮንቴይነሮችን አስተናግዷል፡፡ ከቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ በተገኘው መረጃ መሠረት 2 ሺህ 711 ባለ 20 ጫማና 355 ባለ 40 ጫማ ኮንቴይነሮችን ነው ማስተናገድ የተቻለው፡፡
የባለሀብቶችን ጉዳይ ሲያስፈጽሙ ያገኘናቸው ጌታዬ ጸጋ እና ጌታቸው ኑርልኝ የደንበኞቻቸው ጉዳይ በሞጆና በኮምቦልቻ ይፈጸም እንደነበር ተናግረዋል፡፡ የወረታ ደረቅ ወደብ ግን በቅርበት፣ በአጭር ጊዜና በዝቅተኛ ወጪ እንዲገለገሉ አድርጓቸዋል፤ ንብረታቸውን በፍጥነት እንዲረከቡም በማድረግም ባለሀብቶችን አስደስቷል ነው ያሉት፡፡ ነገር ግን የመንገድ ብልሽት (በተለይ ከጋሸና እስከ ወረታ) መኖሩን እና የተርሚናሉ አቧራ ሸቀጦችን ለጉዳት ማጋለጡን በችግር አንስተዋል፡፡ እንደሌሎች የኢትዮጵያ ደረቅ ወደቦች ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲስተካከልም ጠይቀዋል። ካለው እንቅስቃሴ አንጻርም የማስፋፊያ ሥራው ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል አስተያየታቸውን ለአብመድ የሰጡ የአስመጪና ላኪ እንደራሴዎች፡፡
ሥራ አስኪያጁ በሠጡት ምላሽ ደረቅ ወደቡ አቧራ የሆነው ጊዜያዊ በመሆኑ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በተሟላ መልኩ ማስፋፊያ ሲሠራለት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንደሚገነባም አመላክተዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ያለው እንቅስቃሴ ከቀጠለ በጊዜያዊ ተርሚናሉ ማስተናገድ እንደማይቻል በመናገርም የማስፋፊያ ሥራውን አስፈላጊነት አመላክተዋል፡፡
ማስፋፊያውን ለማከናወንም ጥናት መሠራቱን ነው የወረታ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ሥራ አስኪያጁ ያመላከቱት፡፡ ምንም እንኳን ይህንን ይበሉ እንጂ ማስፋፊያው መቼ እንደሚሠራ ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ አሁን ባለው አቅም ተርሚናሉ 973 ኮንቴይነሮችን መሬት ላይ በማሳረፍ፣ ወደላይ በመደርደር ደግሞ 1 ሺህ 950 ኮንቴይነሮችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚያስችል አቅም አለው።
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article‹‹የአማራ ክልል መሪዎችና ባለሀብቶች ማሽን ከሌላ ክልል አስመጥቶ መሥራት ሊሰማን ይገባል›› ርእሰ መስተዳደር አገኘሁ ተሻገር
Next articleየመጨረሻው የዘመቻው ምዕራፍ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አስታወቁ፡፡