
‹‹የአማራ ክልል መሪዎችና ባለሀብቶች ማሽን ከሌላ ክልል አስመጥቶ መሥራት ሊሰማን ይገባል›› ርእሰ መስተዳደር አገኘሁ ተሻገር
ባህር ዳር: ኅዳር 16/2013 (አብመድ) የአማራ ክልል የግብርና ሜካናይዜሽን ካለው የማምረት አቅም በእጅጉ ያነሰ መሆኑን የክልሉ ግርና ቢሮ አስታወቀ፡፡ የቢሮው ኃላፊ መለስ መኮንን (ዶክተር) እንዳሉት ክልሉ ከ4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የሚታረስ መሬት አለው፡፡ የሀገሪቱን 35 በመቶ ስፋት የሚሸፍን ሲሆን 33 በመቶ ምርት እንደሚሸፍንም ተናግረዋል፡፡ ከሚታረሰው መካከል 80 በመቶው ለዘመናዊ የግብርና አሠራር ምቹ ነው፡፡ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታሩ ደግሞ ለዘመናዊ የሰብል ስብሰባ ምቹ ነው፡፡
ይሁን እንጂ እስካሁን በትራክተር የሚታረሰው ከስድስት በመቶ አይበልጥም፡፡ በክልሉ በትራክተር የሚታረሰውን መሬት ለማዳረስ በየዓመቱ 2 ሺህ 660 ትራክተሮችን ሥራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል፡፡ እስካሁን እየሠሩ የሚገኙት ግን 689 ትራክተሮች ብቻ ናቸው፡፡ በየዓመቱ 267 ኮምባይነሮችን ማቅረብ ቢጠይቅም 10 ብቻ በክልሉ እንደሚገኙ የቢሮው ኃላፊ ጠቅሰዋል፡፡ 57 በመቶ የሚታረስ መሬት ለዘመናዊ ሰብል መሰብሰቢያ ማሽን (ለኮምባይነርና ሀርቨስተር) ምቹ ቢሆንም እስካሁን በዘመናዊ መሰብሰቢያ የሚሰበሰበው 1 በመቶ እንኳን አይሞላም፡፡
ይሕም በምርት ጥራትና ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ የግብርና ምርቶችን በማቀነባበር የተሰማሩ በርካታ ፋብሪካዎች ደረጃውን የጠበቀ ምርት ባለማግኘታቸው ምርቶችን ከሌሎች ክልሎች እንደሚያስገቡ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የግብርና ምርት ጥራትንና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት ይሠራል ብለዋል ዶክተር መለስ መኮንን፡፡
የፌዴራል መንግሥት የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማሳደግ ለአርሶ አደሮች፣ ሕብረት ሥራ ማኅበራት፣ ዩኒየኖችና ልዩልዩ ባለሀብቶች የዕርሻ መሳሪያዎችን ከቀረጥ ነጻ እንዲያቀርቡ ፈቅዷል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ70 በ30 የብድር አገልግሎት እንዲሰጥ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ ይሕንን ተከትሎም በሁሉም ዞኖች ከ250 በላይ አርሶ አደሮች ትራክተርና ኮምባይነር ለመግዛት አስፈላጊውን መስፈርት አሟልተዋል ተብሏል፡፡ የተገዙ መኖራቸውን የገለጹት የቢሮው ኃላፊ ቀሪዎቹም በግዥ ሂደት ላይ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ በአርሶ አደሮች ተገዝተው ዛሬ በባሕር ዳር ርክብክብ የተደረጉት የዚህ አካል መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ማሽኖቹን የገዙት ሦስት የምሥራቅ ጎጃም ዞን ባሶ ሊበን ወረዳና ሁለት የምዕራብ ጎጃም ዞን ወንበርማ ወረዳ አርሶ አደሮች ናቸው፡፡ ምንም እንኳን በቁጥር ትንሽ ቢሆኑም የክልሉን የሜካናይዜሽን ችግር በመፍታት እንቅስቃሴው ፋና ወጊ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ኮምባይነሮቹ የማጨድ፣ የመውቃት፣ ምርትን ከገለባው የመለየትና እስከ 42 ኩንታል ምርትን በመከዘን እንደ ጎተራ የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸው ኮምባይነሮች በአንድ ጊዜ 5 ነጥብ 2 ሜትር በመሸፈን ምርት የመሰብሰብ አቅም አላቸው፡፡ በቀን ከ1 ሺህ እስከ 1 ሺ 500 ኩንታል ሰብል ይሰበስባሉ፡፡
ማሽኖቹን ለማቅረብ በክልሉ መንግሥት ውክልና የተሰጠው አንባሰል የንግድ ሥራዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ገዝቶ አቅርቧል፡፡ በድርጅቱ የአቅርቦትና ሽያጭ ዘርፍ ተወካይ ሽፈራው መኳንንት አምባሰል የግብርና ዘርፉን ለማዘመን የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውን እንደቆየ አመላክተዋል፡፡ በቀጣይም የክልሉ መንግሥት በሚሰጠው ውክልና መሠረት ዘርፉን በማዘመን በምርትና ምርታማነት ላይ የራሱን ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር የአማራ ክልል ግብርና በሚገበው መጠን እንዳላደገ አንስተዋል፡፡ ምርታማነትን በማሳደግ ከውጪ የሚገባን የግብርና ምርት ለማስቀረት መንግሥት በትኩረት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም አርሶ አደሮችን የግብርና ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ማድረግ ይፈለጋል ብለዋል፡፡ ‹‹የአማራ ክልል መሪዎችና ባለሀብቶች ማሽን ከሌላ ክልል አስመጥቶ መሥራት ሊሰማን ይገባል›› በማለትም የክልሉ መንግሥት ችግሮች እንዲቀረፉ እንደሚስራ ተናግረዋል፡፡ የሕብረት ሥራ ማኅበራትና ዩኔኖች በዘርፉ እንዲሳተፉ ትኩረት ይሰጣልም ብለዋል፡፡ የክልሉን ግብርና ሜካናይዜሽን ለማሳደግ ለሚፈልጉ ባለሀብቶችም ተገቢው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ኮምባይነሮችን የገዙ አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየትም ሰብልን በእጅ መሰብሰብና በእንስሳት መውቃትን በዘመናዊ አሰራር ማስቀረት ምርትን ከብክነት ያድናል ብለዋል፡፡ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በምርት ላይ ጉዳት እንዳያደርስም ጉልሕ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ አቶ ዘላለም ሁነኛው እና አቡን አማኑ በሰጡት አስተያዬት አዋጪ ፕሮጄክት ነድፈው ኮምባይነሮችን እንደገዙ ተናግረዋል፡፡ የክልሉ ግብርና ብዙ እንዳልተሠራበት የገለጹት አርሶአደሮቹ፤ በዚህም የብድር እዳቸውን በመክፈል ተጨማሪ ኮምባይነርና ትራክተር የማስገባት ሀሳብ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ማሽኖችን በመግዛት ሂደቱ መንግሥት ላደረገላቸው ሁለንተናዊ ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ