በማይካድራ የተፈጸመው ጅምላ ጭፍጨፋ በማንነት ላይ ያነጣጠረ አሰቃቂ ወንጀል መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

306
በማይካድራ የተፈጸመው ጅምላ ጭፍጨፋ በማንነት ላይ ያነጣጠረ አሰቃቂ ወንጀል መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ባህር ዳር: ኅዳር 16/2013 (አብመድ) ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም በህወሃት የጽጥታ መዋቅር እና ሳምሪ በተባለ ኢ-መደበኛ ገዳይ ቡድን ጭካኔ በተሞላበት መንገድ የአማራ ብሄር ተወላጆች በግፍ መገደላቸውን አብመድ ከቦታው ተገኝቶ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርትም በትንሹ 600 ሰዎች መገደላቸውን የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ ገልጸዋል፡፡ ሳምሪ የተባለው የትግራይ ወጣቶች መደበኛ ያልሆነ ቡድን ጭፍጨፋውን መፈጸሙን ነው ኮሚሽኑ ይፋ ያደረገው፡፡ በድርግቱ የአካባቢው የፖሊስ እና የሚሊሻ አባላት መሳተፋቸውንም ኮሚሽኑ ይፋ አድርጓል፡፡
ጭፍጨፋው በግልጽ ብሄርን መሰረት ያደረገ መሆኑን የገለጸው ኮሚሽኑ የጉዳቱ ሰለባዎችም ጭካኔ በተሞላበት በዱላ በመደብደብ፣ በጩቤ በመውጋት፣ በገጀራ፣ በመጥረቢያ በመመታት እንዲሁም በማነቅ ሕይወታቸው እንዲያልፍ መደረጉን ይፋ አድርጓል፡፡ ግድያው በጥንቃቄ ተቀነባብሮ የተፈጸመ እንደሆነም ገልጿል፡፡
ጭፍጨፋው በጭካኔ የተፈጸመ እና የጦር ወንጀለኝነት እንደሆነም ኮሚሽኑ አመላክቷል፡፡ ጭፍጨፋው በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የስነ ልቦና ጫና መፍጠሩንም ገልጸዋል፡፡ በአካባቢው ከተፈጸመው ጭፋጨፋ በተጨማሪም ከፍተኛ የአካል ጉዳት መድረሱን ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡ የብዙ ቤተሰብ አስተዳዳሪዎች በመገደላቸው ቤተሰቦቻቸው ለችግር መጋለጣቸውንም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡
ጨፍጫፊ ቡድኑ ያሳደዳቸውን ዜጎች ሌሎች የትግራይ ተወላጆች ለማዳን ጥረት ማድረጋቸውንም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብ ሪፖርቱን በማጠናከር ለሚመለከተው አካል ኮሚሽኑ እንደሚያቀርብ ገልጸዋል፡፡
በዳግማዊ ተሰራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ሀገራት በሌሎች የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ ያለመግባት መርህን ሊያከብሩ ይገባል” ጠቅላይ ሚሊስትር ዐቢይ አህመድ
Next articleየአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ዙሪያ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌለው ተገለፀ፡፡