
የአፋር ክልል የተለያዩ ዞኖችና ከተሞች ለሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ለአማራ ልዩ ኃይልና ለሚሊሻ አባላት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 15/2013 ዓ.ም (አብመድ) በአፋር ክልል ዞን ሶስትና አራት እንዲሁም የሰመራ ዙሪያ ከተሞች ከ5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ በአይነትና በገንዘብ በራያ ግንባር ለተሰለፉት የሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት ድጋፍ አድርገዋል። ከ650 በላይ ፍየልና በግን ጨምሮ የበሬ ሰንጋዎች፣ ስኳር፣መኮሮኒና የፊኖ ዱቄት ይዘው ቆቦ ከተማ ለሚገኘው ሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ አስረክበዋል።
የአፋር ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የድጋፍ አሰባሳቢው ኮሚቴ ተወካይ አቶ አይድህስ አፋኪኤ እንዳሉት የትህነግ ዘራፊ ቡድን በመከላከያ ሰራዊቱና በሃገር ሉዓላዊነት ላይ ጥቃት መሰንዘሩ ከታወቀበት ዕለት ጀምሮ የአፋር ህዝብ ድርጊቱን በማውገዝ ህግና ስርዓት እያስከበሩ ካሉት ሰራዊት ጎን ተሰልፎ ድጋፍ እያደረገ ነው።
የትህነግ ስግብግብ ጁንታ የአፋር ህዝብ ያለውን ሰፊ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ሃብት እንዳይጠቀም ዘርፈ ብዙ ተጽዕኖና ጭቆና ማድረሱን የተናገሩት አቶ አይድህስ መንግስት በዘራፊው ቡድን ላይ እየተገበረ ያለውን ህግ የማስከበር እርምጃ እንደግፈዋለን ብለዋል።
የአማራ ህዝብ በችግራችን ጊዜ በፍጥነት የሚደርስልን ወንድማችን ነው ያሉት የአፋር ክልል የህዝብ ተወካዮች ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን ለተሰለፈው የአማራ ልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት ክብር አለን፤እስከ ትግሉ ፍጻሜም በአጋርነት እንደሚሰለፉ ተናግረዋል፡፡
የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልደትንሳኤ መኮንን በበኩላቸው የአፋር ህዝብ የትህነግን ከሃዲ ቡድን ሃገር የማተራመስ እኩይ አላማን በመረዳት ለሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ለአማራ ልዩ ኃይልና ለሚሊሻ አባላት ድጋፍ ማድረጋቸው እየተከናወነ ላለው ህግ የማስከበር የህልውና ዘመቻ ኢትዮጵያዊያን በህብረት መሰለፋችንን ያሳያል ነው ያሉት።
የትህነግ ከሃዲና ዘራፊው ቡድን በህግ ተጠያቂ እስከሚሆን ድረስ እየተደረገ ያለው ህዝባዊ ድጋፍም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- ስማቸው እሸቴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m