
የኢትዮጵያ እና የቻይና ፕሬዝዳንቶች የሀገራቱን ፍሬያማ የጋራ ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ አስታወቁ፡፡
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 15/2013 ዓ.ም (አብመድ) የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳኅለወርቅ ዘውዴ እና የቻይናው አቻቸው ሺ ጂንፒንግ የሀገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመረበትን 50ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የመልካም ምኞት መልዕክት ተለዋውጠዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ሳኅለወርቅ የኢትዮ-ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላለፉት 50 ዓመታት በጋራ የፖለቲካ መተማመን ላይ በመመስረቱ ፍሬያማ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ ወደ ሁለገብ ስትራቴጂካዊ ትብብር አጋርነት ማደጉንም አድንቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ቻይና ያላቸዉን ግንኙነት በማጠናከር እና ትብብራቸውን በተለያዩ ዘርፎች ማስፋት ለሃገራቱ እና ለህዝብ የጋራ ተጠቃሚነት ያረጋግጣል ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ሳኅለወርቅ በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለውን ባህላዊ ትስስር የበለጠ ለማጎልበት ከፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር ተቀራርበው ለመስራት ጥብቅ ፍላጎት መኖሩን አረጋግጠዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ በበኩላቸው ለግማሽ ምዕተ ዓመት የዘለቀው የቻይና እና የኢትዮጵያ ወዳጅነት ፈተናዎችን ተቋቁሞ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡
በቅርቡ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተቋቋመው ሁለገብ ስትራቴጂካዊ የትብብር አጋርነት የጠበቀ ፖለቲካዊ መተማመን፣ ፍሬያማ ዘርፈ ብዙ ትብብር እና ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት፣ በድጋፍ እንዲሁም በዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ የጠበቀ ትብብር እንዲኖራቸው ያረጋገጠ መሆኑንም አብራተዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በቻይና እና ኢትዮጵያ መካከል የነበረው አብሮነት እና መረዳዳት ለሀገራቸው እና ለተቀረው የአፍሪካ ሀገራት ትብብር በአርዓያነት የሚጠቀስ መሆኑን ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ አንስተዋል፡፡
“ለቻይና ኢትዮጵያ ግንኙነቶች መጎልበት ሁልጊዜም ትልቅ ቦታ እሰጣለሁ” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
ቻይና እና ኢትዮጵያ በይፋ ዲፕሎማሲ ግንኙነትን የጀመሩት (እ.ኤ.አ) ኅዳር 24/1970 እንደነበር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
በየማነብርሃን ጌታቸው