
ወጣቱ ምንጫቸው ባልተረጋገጠ የማኅበራዊ ሚዲያ መረጃዎች ላይ በመጠመዱ የንባብ ባህሉ መቀነሱን የእንጅባራ ከተማ ነዋሪዎቸ ተናገሩ፡፡ “የንባብ ባህላችንን በማዳበር ምክንያታዊ ትውልድ አንፍጠር’’ በሚል መሪ መልዕክትም የንባብ ሳምንት ንቅናቄ በከተማዋ ተጀምሯል፡፡
ባህር ዳር: ኅዳር 15/2013 (አብመድ) ንባብ የአካባቢያችንንና ዓለማችንን እውናዊና ምናባዊ ሁኔታዎችን ለመረዳት፣ የመልዕክት ልውውጥን በትርጉም አዘል የጽሕፈት ስርዓት በመወከል የመልዕክት ላኪና ተቀባይ በሌለበት ቦታና ጊዜ ተግባቦት እንዲፈጠር የሚያስችል ጥበብ ነው፡፡
የራሷ ፊደልና የጽሕፈት ስርዓት ባለቤት በመሆን የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ የዜጎቿ የንባብ ባህል የታሪኳን ያክል አለማደጉ ይነገራል፡፡ ለዚህ ደግሞ የተደራስያንን ቀልብና ስሜት የመግዛት አቅም ያላቸው የስነ-ጽሑፍ ሥራዎች በብዛት አለመኖር፣ የማኅበራዊ ሚዲያ አገልግሎት መስፋፋትና የመጽሐፍት ዋጋ መናር ገና በጅምር የነበረውን የንባብ ባህላችን ሳይጎለምስ እንዲያረጅ አድርገውታል፡፡
እየተቀዛቀዘ የመጣውን የንባብ ባህል ለማነሳሳት ያለመ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የንባብ ሳምንት ንቅናቄም “የንባብ ባህላችንን በማዳበር ምክንያታዊ ትውልድ አንፍጠር’’ በሚል መሪ መልዕክት በእንጅባራ ከተማ አስተዳደር ተጀምሯል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሙሉ ተስፋየ ከህዳር 14 እስከ 21/2013 ዓ.ም በሚካሄደው በዚሁ የንባብ ሳምንት ንቅናቄ የንባብ ባህልን ለማዳበር ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር፤ ከባለሀብቶችና ከለጋሽ ድርጅቶች መጽሐፍትን ማሰባሰብና ተጨማሪ የንባብ ማዕከላትን ለማደራጀት የሚያስችሉ ውይይቶችን የማካሄድ ተግባራት እንደሚከናወኑ ገልፀዋል፡፡
የንባብ ሳምንት መክፈቻ መርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የእንጅባራ ከተማ ነዋሪ ኢንጂነር አክሊሉ መኮንን ወጣቱ ምንጫቸው ባልተረጋገጡ የማኅበራዊ ሚዲያ መረጃዎች ላይ በመጠመዱ ባህሉንና ታሪኩን በውል እንዳይረዳ አድርጓል ብለዋል፡፡ አሁን ያሉት የንባብ ማዕከላት ካለው የሕዝብ ቁጥር አንጻር አነስተኛ በመሆናቸውም የንባብ ማዕከላትን ተደራሽና ዲጂታላይዝ በማድረግ ችግሩን መቅረፍ ካልተቻለ በእውቀት ሽግግር ላይም የራሱ የሆነ አሉታዊ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
ኢንጂነር አክሊሉ በእለቱም ‹‹ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል›› በሚል መርህ 20 ሺህ ብር የሚያወጡ ልዩ ልዩ መጽሐፍትን ገዝተው በእንጅባራ ከተማ ለሚገኘው ቤተ-መጽሐፍት በስጦታ አበርክተዋል፡፡ በእንጅባራ ከተማ በተካሄደው በዚሁ የንባብ ሳምንት መክፈቻ መርሀ ግብርም ከመንግስት ሠራተኞች፣ ከባለሀብቶችና ከከተማው ነዋሪዎች ከ320 በላይ መጽሐፍት በስጦታ ተበርክተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ሳሙኤል አማረ -ከእንጅባራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ