ኢትዮጵያን ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚያስተሳስረው የዲማ – ራድ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ተጠናቀቀ።

216
ኢትዮጵያን ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚያስተሳስረው የዲማ – ራድ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ተጠናቀቀ።
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 15/2013 ዓ.ም (አብመድ) 60 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ፍጻሜውን ማግኘቱ አማራጭ የገቢ ወጪ ንግድን ለማሳለጥ ከፍተኛ ጠቀሜታን ያበረክታል ተብሏል።
የመንገድ ትራንስፖርት ትስስርን ከማቀለጠፉም በላይ ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያላትን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የማህበራዊ እና የኢኮኖሚ እንዲሁም የንግድ ልውውጥን የተሳለጠ ከማድረግ አኳያ የመንገዱ ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
የዲማ – ራድ ድልድይ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ለሀገሪቱ ዋነኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝላትን ቡናን ጨምሮ የፍራፍሬ ፣ ማር እና ቅመማ ቅመም ምርት ውጤቶችን ከምዕራቡ የሀገሪቷ ክፍል ወደ ውጪ በመላክ ሀገራዊ ሚናው የጎላ ከመሆኑም በላይ በአካባቢው ያሉትን አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል ነው የተባለው፡፡
መንገዱ በሚያካልላቸው ከተሞች ፣ የእርሻና የኢንዱስትሪ ዞኖች እንዲሁም የቱሪስት መስህብ የሆኑ ስፍራዎችን ዘመናዊ በሆነ መንገድ በማስተሳሰር የጉዞ ጊዜንና ወጪን በመቀነስ ረገድ ፋይዳው የጎላ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
መንገዱ ከዚህ ቀደም ለትራንስፖርት አመቺ ያልሆነ የተጎዳ ጠጠር መንገድ የነበረ ሲሆን መስመሩ ሊያበረክተው ከሚችለው ፋይዳ አኳያ ወደ አስፋልት ኮንክሪት ደረጃ እንዲያድግ መደረጉ ተመልክቷል፡፡
ፕሮጀክቱን በኢትዮጵያ መንግስት በተመደበ 856 ሚሊዮን ብር ገንብቶ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ነው። የማማከር እና የቁጥጥር ስራውን ያከናወነው ደግሞ የኢትዮጵያ ዲዛይንና ቁጥጥር ስራዎች ኮርፖሬሽን ነው፡፡
የደቡብና ጋምቤላ ክልልን የሚያገናኘው የዚሁ የመንገድ ትስስር አካል የሆነው የሚዛን ዲማ የመንገድ ፕሮጀክትም በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በይፋዊ ገጹ አስፍሯል።
ፕሮጀክቱ 91 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመትን ይሸፍናል። ለፕሮጀክቱ የሚውለው 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የሚሸፈነው በኢትዮጵያ መንግስት ነው። የመንገድ ግንባታውን እያከናወነ የሚገኘው MCC17 የተባለ የቻይና አለምዓቀፍ የስራ ተቋራጭ ድርጅት ነው። የማማከሩን ተግባር ደግሞ የህንዱ አርቪ አሶሲዬት ኮንሰልታንሲ ከኢትዮጵያው አማካሪ ድርጅት ኔት ጋር በጋራ እየሰሩ መሆኑ ተገልጿል።
Previous articleበንጹኃን ዜጎች ላይ ግድያ የሚፈጽሙ ሽፍቶችን በመከታተል አካባቢያቸውን እየጠበቁ መሆኑን በዚገም ወረዳ የሚኖሩ የጉሙዝ ተወላጆች ተናገሩ፡፡
Next articleየትህነግ ዘራፊ ቡድን ሲጠቀምበት የነበረ 32 ኩንታል አደንዛዥ እፅ በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡