
በንጹኃን ዜጎች ላይ ግድያ የሚፈጽሙ ሽፍቶችን በመከታተል አካባቢያቸውን እየጠበቁ መሆኑን በዚገም ወረዳ የሚኖሩ የጉሙዝ ተወላጆች ተናገሩ፡፡
ባህር ዳር: ኅዳር 14/2013 (አብመድ) በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዚገም እና ጓንጓ ወረዳዎች የጉሙዝ ብሔረሰብ ተወላጆች ከሌላው ማኅበረሰብ ጋር ተሳስበው፣ ተቻችለው በሰላም ይኖራሉ፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን እየተፈጠረ ያለው የሰው ህይወት መጥፋት እንደሚያሳስባቸውም ተናግረዋል፡፡ በመተከል የደረሰው ግድያ ወደ ብሔረሰብ አስተዳደሩም እንዳይከሰት አካበቢያቸውን በንቃት እየጠበቁ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
አብመድ ካነጋገራቸው የጉሙዝ ብሔረሰብ ተወላጆች መካከል አቶ ኡማ ክላንጃ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዚገም ወረዳ ለረጅም ዓመታት ከማኅበረሰቡ ጋር በፍቅር ነው እየኖሩ ያሉት፡፡ አቶ ኡማ እንደሚሉት በሚኖሩበት አካባቢ እስከ አሁንም ጉሙዝ በመሆናቸው ምንም ችግር ደርሶባቸው አያውቅም፡፡ ከማኅበረሰቡ ጋር ተሳስበው እንደሚኖሩ አስረድተዋል፡፡ የአካባቢውን ፀጥታ ለመረበሽ የሚመጡ ሽፍቶች ሲኖሩም ለፀጥታው አካል ጥቆማ በማድረስ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በአጎራባች የመተከል ዞን በጊዜያዊ ጥቅም የተደለሉ ሽፍቶች ታይቶ በማይታወቅ አኳኋን በህፃናት፣ በእናቶች፣ በአዛውንቶች እና በሃይማኖት አባቶች ላይ ግድያ በመፈጸማቸው እንዳሳዘናቸውም አቶ ኡማ ተናግረዋል፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪ የጉሙዝ ብሔረሰብ ተወላጅ አቶ ናሚ ወድም እንዳሉት እንደ ቀደምት አባቶች ሁሉም ዜጋ ተከባብሮ እና ተሳስቦ መኖር አለበት፤ “እኛም የታሪክ ተጠያቂ እንዳንሆን የአባቶችን ምክር ተቀብለን ከሌላው ብሔር ልዩነትን ውበት አድርገን ነው የምንኖረው”ብለዋል፡፡
ተልዕኮን በመቀበል እና በማስፈጸም በንጹኃን ዜጎች ላይ ግድያ የሚፈጽሙ ሽፍቶችን በመከታተል አካባቢያቸውን እየጠበቁ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በአካባቢያቸው ችግር እንኳን ሲፈጠር በጋራ በመወያየት መፍትሔ እንደሚያበጁለት ነግረውናል፡፡ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በተለያዩ ማኅበራዊ ሁነቶች ሳይለያዩ እየኖሩ እንደሆነም አቶ ናሚ አስረድተዋል፡፡
በሌሎች አካባቢዎች የታየው ሞት እና መፈናቀል እንደሚያሳስባቸውም ገልጸዋል፤ በአካባቢያቸው መሰል ችግር እንዳይፈጠር ከወረዳው የአስተዳደር አካላት፣ ከሴቶች፣ ከወጣቶች፣ ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በቅንጅት እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
የዚገም ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ገበየሁ አልማ እንደገለጹት የዚገም ወረዳ ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ እና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር ስለሚዋሰን ኅብረተሰቡ በጋራ የአካባቢውን ሠላም ማስጠበቅ የሚችልባቸውን ስልቶች በተመለከተ ግንዛቤ መፈጠሩን አብራርተዋል፤ የፀጥታውን ሃይል በሚገባ በማደራጅት እና የስጋት ቀጣናዎችን በመለየት ጠንካራ የአመራር ስምሪት እየተጠሰ እንደሚገኝ ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡-አዳሙ ሽባባው
ፎቶ፡- በዚገም ወረዳ የመንግስት ኮሙዩንኬሽን
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ