
የታላቋ ከተማ አዲስ የተስፋ ብርሃን!
ባህር ዳር: ኅዳር 14/2013 (አብመድ) በደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ለዘመናት የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ችግር መፈታት የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን በከፍተኛ ደረጃ እያነቃቃው እንደሆነ የከተማ አስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ይኖራቸዋል ተብለው ተስፋ ከተጣለባቸው የአማራ ክልል ከተሞች መካከል ደብረታቦር አንዷ ናት።
የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች መኖር፤ የተማረ የሰው ኃይልና ምቹ የአየር ንብረት ባለቤት መሆኗ ደግሞ ከተማዋን ተመራጭ ያደርጋታል። በኢንቨስትመንቱ የመልማት ዕድል ያላገኘችው ከተማዋ በሥራ አጥነት ተፈትናለች። ለዚህ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የኤሌክትሪክ ኃይል ችግር እንደነበር የከተማ አስተዳደሩ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
የመሠረተ ልማቶች አለመሟላትና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችም ቀደም ባሉት ጊዜያት ዘርፉ ትኩረት ተነፍጎት እንደነበር ማሳያዎች ናቸው። በኃይል እጥረት ምክንያት ፈተና ካጋጠማቸው ኢንዱስትሪዎች መካከል በጌ ምድር የዱቄት ፋብሪካ አንዱ ነው፡፡ ፋብሪካው በከተማዋ የመጀመሪያና ፈር ቀዳጂ ሲሆን ግንባታው የተጀመረው በ2005 ዓ.ም ነው፡፡ በ2008 ዓ.ም ግንባታው ተጠናቅቆ ለሥራ ዝግጁ ቢሆንም በኃይል እጥረት ምንንያት በ2009 ዓ.ም ነበር ሥራ የጀመረው፡፡ እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ በኃይል እጥረትና መቆራረጥ ተፈትኖ እንደነበር የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ ከድር መሐመድ ተናግረዋል። ከ300 ቮልቴጅ በታች በሆነ ኃይል በመጠቀሙም ማሽኖች ለብልሽት መጋለጣቸውን ተናግረዋል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል 6 ነጥብ 5 ሜጋዋት ብቻ ነበር፡፡ ኢንዱስትሪዎችን ማንቀሳቀስ ባለመቻሉ ፋብሪካዎች ተፈትነው እንደነበርም የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አጉማሴ ገበየሁ አስታውቀዋል፡፡ ችግሩ በ2012 ዓ.ም መፍትሔ አግኝቷል፡፡ ባለ 50 ሜጋ ዋት ተንቀሳቃሽ ሰብስቴሽን ተሠርቷል፤ የከተማዋ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅምም ወደ 56 ነጥብ 5 ሜጋ ዋት አድጓል ብለዋል፡፡
አሁን በጌምድር ዱቄት ፋብሪካ ከ380 ቮልቴጅ በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል በመጠቀም በሙሉ አቅሙ እየሠራ ነው፤ ሌሎች ፋብሪካዎችም በፈረቃ ከመሥራት ተላቅቀው በጥሩ የሥራ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ፡፡ ችግሩ መፈታቱ የከተማዋን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ አነቃቅቶታል፡፡ ከ9 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት ያስመዘገቡ 52 ባለሀብቶች በተለያዩ ዘርፎች ተሠማርተዋል፡፡ ከ820 በላይ ሰዎችም የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡
ይሁን እንጂ በሙሉ አቅማቸው ሥራ ሲጀምሩ የግብዓት እጥረት አጋጥሟቸዋል፡፡ ይህም በተመሳሳይ ዘርፍ የተሠማሩ ፋብሪካዎች፣ ከአርሶ አደሮች ጋር ትሥሥር አለመፍጠራቸውና ግብርናው በቂ አቅርቦት እንዲኖረው የሚያስችል ሥራ አለመፈጠሩ በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከመስጠት ባሻገር አስተማማኝ ግብዓት እንዲኖር ትኩረት ሰትቶ ሊሠራ እንደሚገባም ባለሀብቶች ተናግረዋል፡፡ የውሃና የመንገድ መሠረተ ልማት ችግር እንዲስተካከልም ጠይቀዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት እየሠራ ይገኛል፡፡ የጽህፈት ቤት ኃላፊው እንደተናገሩት በተለይ የአገልግሎት ዘርፉ እምብዛም ያልተሠራበት በመሆኑ በመንገድ ዳርቻ ላይ ያሉ የመንግሥት ተቋማትን በማንሳት ለባለሀብቶች እንዲተላለፍ ተወስኗል፡፡ በአምራች ዘርፉ ለመሠማራ ቦታ ወስደው ፈጥነው ሥራ ያልጀመሩትን በመንጠቅም ለተሻለ ባለሀብት እየተሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ከመንገድና ከውሃ ጋር የሚነሱ ችግሮችን የማስተካከል ኃላፊነት የተሰጠውና ኢንዱስትሪ መንደሮችን የሚስተዳድረው የክልሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ጽህፈት ቤት በመሆኑ ችግሩ እንዲፈታ በጋራ እንደሚሠራ አመላክተዋል፡፡ የግብዓት እጥረት ችግሮችን ለመፍታት የግብርና ምርቶችን ለማሳደግ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ነው ያመላከቱት። ለዚህም የሥራ ኃላፊዎች ቅንጅታዊ አሠራር ያስፈልጋል ብለዋል የጽሕፈት ቤት ኃላፊው፡፡ በተመሳሳይ ዘርፎች የሚኖረውን ኢንቨስትመንት በተመረጡ ሌሎች ዘርፎች ላይ በማሳተፍ የግብዓት እጥረቱን ለመቀነስ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ