አርሶ አደሮች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የለም በሚል ሰብል ስብሰባ ላይ እንዳይዘናጉ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አሳሰበ፡፡ በክልሉ እስከአሁን በዘር ከተሸፈነው 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታሩ መሰብሰቡም ታውቋል፡፡

743
አርሶ አደሮች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የለም በሚል ሰብል ስብሰባ ላይ እንዳይዘናጉ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አሳሰበ፡፡
በክልሉ እስከአሁን በዘር ከተሸፈነው 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታሩ መሰብሰቡም ታውቋል፡፡
ባህር ዳር: ኅዳር 14/2013 (አብመድ) የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱና በአግባቡ በመሰብሰብ የምርት ብክነት እንዳይፈጠር አርሶ አደሮች ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስገንዝቧል፡፡
ከአብመድ ጋር በስልክ ቆይታ የነበራቸው የባሶ ሊበን ወረዳ የዶገም ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ደምል ሀበሻ የደረሱ ሰብሎችን በደቦና በኮምባይነር ተጠቅመን እየሰበሰብን ነው ብለዋል፡፡ በባሶ ሊበን ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የሰብል ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ሙሉቀን አለሙ የደረሱ ሰብሎችን በአግባቡ ለመሰብሰብ ኮምባይነሮች ወደ ወረዳው ገብተው የሰብል ስብሰባና ውቂያ እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ምርቱ ወደ ቤት ከገባ በኋላ በተባይ እንዳይበላ ለመከላከል አርሶ አደሮች ተባይ የሚከላከሉ ኬሻዎችን እንዲጠቀሙ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡ ህግ ለማስከበር ወደ ግንባር የተንቀሳቀሱ የሚሊሻ አባላት ሰብልም በደቦና በማህበር እየተሰበሰበ መሆኑን አቶ ሙሉቀን ጠቅሰዋል፡፡
የምስራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ እምቢያለ አለኸኝ በዞኑ ሰሊጥ፣ ስንዴ፣በቆሎ፣ጤፍና ገብስ በብዛት የሚመረቱ ሰብሎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ አርሶ አደሮች የደረሱ ሰብሎችን በባህላዊ እና በዘመናዊ መንገድ እየሰበሰቡ ነው ብለዋል፡፡ የህወሓት ህገወጥ ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የከፈተውን የጥፋት ዒላማ ለመቀልበስ የሚለሻ ኃይል ወደ ሰሜን ማቅናቱ ይታወቃል፡፡ የሚለሻ ኃይሉ ምርት እንዳይባክንም በየቀበሌው የቀሩ አርሶ አደሮች አደረጃጀቶችን ተጠቅመው ምርቱን የሚሰበስቡበት ሁኔታ መፈጠሩን ነግረውናል አቶ እምቢያለ፡፡
የምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ሰውመሆን ተገኘ በበኩላቸው ቀድመው የደረሱ እንደ ገብስ ቦለቄና ባቄላ የመሳሰሉ ሰብሎች ተሰብስበዋል፤ እስካሁንም በሰብል ከተሸፈነው 487 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 28 በመቶ ያህሉ መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሩ ከመዘናጋት ወጥቶ የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ በመሰብሰብና ወደ ጎተራ በማስገባት በሰብል ስብሰባ ወቅት የሚከሰትን የምርት ብክነት ሊከላከል እንደሚገባም አቶ ሰውመሆን አሳስበዋል፡፡
በአማራ ክልል በ2012/2013 የመኸር እርሻ 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 127 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን በክልሉ የሰብል ልማትና ጥበቃ ባለሙያ ወይዘሮ እንዬ አሰፋ ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሮች የደረሱ ሰብሎችን በደቦ፣ በማህበርና ዘመናዊ ማሽኖችን በመጠቀም እየሰበሰቡ ነው፤ እስካሁንም በዘር ከተሸፈነው 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታሩ ተሰብስቧል፡፡ ከተሰበሰቡ ሰብሎች ውስጥ ገብስ፣ ሰሊጥ፣ ማሾ፣ ማሽላና ጤፍ ይገኙበታል ብለዋል ወይዘሮ እንዬ፡፡ በብዛት ስንዴ በሚመረትባቸው የምስራቅ ጎጃም ዞን የተለያዩ ወረዳዎች 47 ያህል ኮምባይነሮች ገብተው እየሰበሰቡ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የምርት ብክነት እንዳይከሰት አርሶ አደሮች ዘመናዊ ማከማቻዎችን እንዲጠቀሙ ግንዛቤ እየተፈጠረ መሆኑን ነግረውናል፡፡ የመከላከያ ሰራዊትን ለማገዝ ወደ ሰሜን ያቀንው የሚሊሻ ኃይል ምርቱ እናዳይባክን አደረጃጀቶችን በመጠቀም ምርቱ እየተሰበሰበ መሆኑን ወይዘሮ እንዬ አስረድተዋል፡፡ አርሶ አደሮች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የለም በሚል ሰብል ስብሰባ ላይ እንዳይዘናጉ ያሳሰቡት የክልሉ የሰብል ልማትና ጥበቃ ባለሙያዋ ቀሪውን ሰብል በወቅቱ መሰብሰብ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
42
Previous articleከሚያመርተው 80 በመቶውን ለውጪ ገበያ ለማቅረብ አቅዶ ወደ ስራ የገባው ፋብሪካ ስኬታማ መሆን አልቻለም፡፡
Next article