
ከሚያመርተው 80 በመቶውን ለውጪ ገበያ ለማቅረብ አቅዶ ወደ ስራ የገባው ፋብሪካ ስኬታማ መሆን አልቻለም፡፡
ባህር ዳር: ኅዳር 14/2013 (አብመድ) በዓባይ ኢንዱስትሪያል አክሲዮን ማኅበር አማካኝነት ጎንደር ላይ የተገነባው የአልባሳትና ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ በ2012 ዓ.ም ነበር ወደ ማምረት የገባው። ፋብሪካው የጂንስ ሱሪ፣ ሸሚዝ፣ ካኪ፣ ሹራብና ልዩ ልዩ አልባሳትን ያመርታል።
ይሁን እንጂ የፋብሪካው የምርት እንቅስቃሴም ሆነ የግብይት ሁኔታ በታቀደው ልክ ስኬታማ አልነበረም። ወደ ማምረት ሲገባም በሙሉ አቅሙ ከሚያመርተው 80 በመቶውን ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ነበር። በዕቅዱ መሠረትም እስካሁን ምርቶቹን ለውጪ ገበያ ማቅረብ ነበረበት።
ይሁን እንጂ ማምረት በጀመረበት ወቅት የኮሮና ቫይረስ በመከሰቱ ምርቱን ለውጪ ገበያ ማቅረብ እንዳልቻለ የዓባይ ጋርመንት ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ማናየሽ ተሰማ አስታውቀዋል። ፋብሪካው በሦስት ሸዶች ሌሎች ደጋፊ ማሽኖችን ሳይጨምር ከ1 ሺህ 200 በላይ የልብስ ስፌት ማሽኖች አሉት።
ይሁን እንጂ በዚህ ጊዜ ሥራ ላይ የዋሉት ማሽኖች ከ700 አይበልጡም። ከሦስቱ ሸዶች መካከል በሁለቱ ውስጥ የማሽን ተከላ ሥራ አልተጠናቀቀም። ኮንትራቱን የያዙት የውጪ ሀገራት ድርጅቶች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ አለመግባታቸውም በምክንያትነት ተነስቷል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ፋብሪካው የተቀጠሩ ሠራተኞችን ማቆየት በሚያስችል የምርትና የሀገር ውስጥ የግብይት እንቅስቃሴ ላይ መወሰኑን ነው ሥራ አስኪያጇ የተናገሩት።
በአሁኑ ጊዜ ፋብሪካው በቀን ከ26 ሺህ በላይ የተለያዩ አልባሳትን ማምረት የሚያስችል አቅም ቢኖረውም ከትምህርት ሚኒስቴር በደረሰው ጥሪ መሠረት የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል በማምረት ለትምህርት ተቋማት እያስረከበ እንደሚገኝ ተገልጿል። በቀን እስከ 30 ሺህ ዓለም ዓቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የማክስ ምርት በማዘጋጀት በተለይ ለዩኒቨርሲቲዎች እንደሚያስረክብም ሥራ አስኪያጇ ተናግረዋል።
ማሽኑን ለመትከል ስምምነት የወሰዱ ድርጅቶች ቀርበው ማሽን ተከላውን ሲያጠናቅቁ፣ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተቀዛቀዘው የንግድ እንቅስቃሴ ሲያንሠራራና የአልባሳትና ጨርቃጨርቅ ዘርፉ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ የተሻለ የሥራ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል። ምርቶቹን በበቂ ሁኔታ ለውጪ ገበያ በማቅረብም ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ያስገኛል ብለዋል ወይዘሮ ማናየሽ።
ችግሩን ለመፍታት እንቅስቀሴ መጀመሩን ያስታወቁት ወይዘሮ ማናየሽ በምን ያህል ፍጥነት እንደሚጠናቀቅ ግን እርግጠኛ አልሆኑም። ለውጪ ሀገራት ባለሙያዎች ጥገኛ የሆነው ፋብሪካ በታቀደው መሠረት እንዲገባ ባለሙያዎቹን መጠበቅ ግድ ሆኖበታል። ፋብሪካው አሁን ባለው ቁመና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለተመረቁና በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርታቸውን ላልጨረሱ ከ650 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ ዕድል ፈጥሯል። በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምርም ደግሞ ከ3 ሺህ በላይ ሠራተኞችን ማስተናገድ የሚያስችል አቅም እንዳለው ታውቋል።
ወደ ምርት ከመግባቱ አስቀድሞም በጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፉ ዓለምአቀፍ እውቅና ካላቸው እንደ ቬትናም፣ ባንግላዲሽ፣ ሲሪላንካና ሌሎች ሀገራት ባለሙያዎችን በማስገባትም ከ650 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች በቂ የሙያ ስልጠና መስጠቱን አብመድ ማወቅ ችሏል።
ለሀገር ውስጥ ባለሙያዎች የቴክኖሎጂ እውቀት ሽግግርን እንዲኖር በማድረግም የውጪ ሀገራት ባለሙያዎችን ተክተው እንዲሠሩ ተደርጓል። ከተቀጠሩት መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት የስፌት ባለሙያዎች ናቸው። በስፌት ሥራው ከተሠማሩት 99 በመቶ ሴቶች ሲሆኑ የ10ኛ ክፍል ትምህርታቸውን አጠናቅቀው የሥራ ዕድል ሳያገኙ የቆዩም ይገኙበታል።
የሥራ ዕድሉ ተጠቃሚዎችም በሥራቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። የሹራብ ምርት ቡድን መሪዋ ትዕግሥት ዐቢይ በ2009 ዓ.ም ከዩኒቨርስቲ ከተመረቀች በኋላ እስከ 2012 ዓ.ም ያለሥራ ቆይታለች። በዚህ ጊዜም ከፍተኛ የስነልቦና ጫና ውስጥ ገብታ እንደነበር ነው የተናገረችው። ሥራ ከጀመረች ከአንድ ዓመት በላይ የሆናት ትዕግስት ከደረሰባት ሥነልቦናዊ ጫና በመውጣት ጥሩ ሙያዊ ክህሎት ማግኘቷን ነግራናለች። ሌሎች ሀሳባቸውን ለአብመድ የሰጡ የድርጅቱ ሠራተኞችም በተፈጠረላቸው የሥራ እድልና ባገኙት ሙያዊ እውቀት ተደስተዋል። አስተያየታቸውን ከሰጡት ተቀጣሪዎች መካከል የሚከፈላቸው ወርሃዊ ደመወዝ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ሁኔታ ያላገናዘበ መሆኑን አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ