
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በሕግ ማስከበር ተልዕኮው የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ባለፉት ጥቂት ቀናት ያስመዘገበው ድል የሚደነቅ ነው ብለዋል።
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 12/2013 ዓ.ም (አብመድ) ሠራዊታችን ትናንት ምሽት በአዲግራት ዙሪያ ያሉትን አካባቢዎች ከተቆጣጠረ በኋላ፣ ዛሬ ደግሞ አዲግራትን ከሕወሓት ኃይል ሙሉ በሙሉ ነፃ አውጥቷል ነው ያሉት።
የፌደራል መንግሥት በተቆጣጠራቸው ከተማዎችና አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች፣ በጸጥታ ኃይሎች ጥበቃ እየተደረገላቸው ወደ ዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው መመለስ ጀምረዋል። ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመሆን፣ ሰብአዊና ማኅበራዊ ፍላጎቶች የሚሟሉበት መንገድ እንደሚመቻች ገልፀዋል።
የሰብአዊ ድጋፍ ክንውኖችን ለመከታተል በፌደራል መንግሥት የተዋቀረው ከፍተኛ ኮሚቴ፣ ተመጣጣኝ እና ወቅታዊ ድጋፍ ለማቅረብ የሚያስችል መረጃን እንዲያሰባስቡ ተጨባጭ ሁኔታውን የሚያጣሩ ልዑካንን ወደ ስፍራው ልኳል። በተጨማሪም፣ ይህ ኮሚቴ ባለፉት ቀናት መኖሪያቸውን ጥለው የተሰደዱትን ዜጎች ሁሉ ወደ ቀያቸው ለመመለስ እና ለማቋቋም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር መሥራቱን ይቀጥላል ብለዋል።
የፌደራል መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ አጠቃላይ ደኅንነት እና ጤንነት ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጥ ስለ ሆነ፣ በትግራይ ክልል መረጋጋት እንዲሰፍን እና ዜጎቻችን ከጉዳት እና እጦት ነፃ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋዊ ገፃቸው አመላክተዋል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ