
‹‹ የልዩ ኃይሉና የሚሊሻው ልዩ ገድል››
በሀገሩ የማይደራደር፣ ከጥቀምኛ ጋር የማያብር፣ የጠላት ምሽግ በደቂቃዎች የሚሰብር፣ ለጠላት የማይበገር ነው፡፡ ‹‹የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳል›› እንዲሉ ትህነግ የፈራው እየደመሰሰው፣ የጠላው እያፈራረሰው ነው፡፡ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ጠልቶ በኢትዮጵያ መኖር እንዴትስ አሰቡት ?
በሠላም ቀን አራሽ በክፉ ቀን ተኳሽ የሆነው የአማራ ሚሊሻ መከታህ ተነካ ሲባል እንደወጣ አሁንም በበረሃ ላይ ነው፡፡ ሀገር እንዳይራብ እያረሰ፣ ድንበርና ክብር እንዳይገፋ እየተኮሰ የኢትዮጵያ ዋልታ ሆኖ ዘልቋል፡፡ አሁንም ለኢትዮጵያ የተደገሰባትን ሞት በድል እየተወጣ፣ ኢትዮጵያዊነትን የደፈረውን እያባረረ ወደፊት እየገሰገሰ ነው፡፡ ጠቡ ከማንም ጋር አይደለም፤ እናት ሀገሩን ከሚደፍር፣ ሕዝቦችዋን ከሚያሳፍር፣ ኢትዮጵያን አብዝቶ የሚወድ ሁሉ ጠላቴ ነው ከሚል ጥቅመኛ ጋር ነው፡፡
ልዩ ኃይሉ ልዩ ገድል እየፈፀመ ነው፡፡ የአማራ ሚሊሻ ጠላትን መድረሻ አሳጥቶታል፡፡ በሌሊት ተነክቶ በሌሊት ግንባር መትቶ ነው የመለሰው፡፡ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ታጋሽ ነው ቶሎ አይሞቅም፣ ብርቱ ነው በቀላል ነገር አይወድቅም፣ ደፋር ነው ጉድብ አይለቅም፣ ፈጣን ነው አባሮ አይለቅም፣ ካልነኩት አይነካም ከነኩት አይመለስም፤ ይህ የኖረበት መገለጫው ነው፡፡ ጠላቱ የሀገርና የሕዝብ የሆነው ቡድን ነው፤ ትህነግ እንደሚለው ሕዝብን አይወጋም፡፡ በልዩ ኃይሉና በሚሊሻው አመካከትና አጠቃቅ የጦር አዛዦችን ጨምሮ የጦር ሜዳ ጓዶች ይሄስ ግሩም ድንቅ ብለውለታል፡፡
የጦር ሜዳ ጓዶች የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ከባድ የተባለውን ምሽግ ሰብረው ለማለፍ ይሽቀዳደማሉ ይሏቸዋል፡፡ በየትኛውም የውጊያ ስልት የተቀኙና የተካኑ ናቸው ነው የሚሏቸው፡፡ ለዓመታት የተዘጋጄን ጉድብ በሰዓታት ዶግ አመድ አድርገው ለሌላ ድል ይዘጋጃሉ፡፡ አማራ ሀገር እንዳይራብ አራሽ፣ ወገን እንዳይጠቃ ተኳሽ ነው፡፡ ለዚህ ምስክር የአማራ ሚሊሻ በብርዳም ክረምት ሲያርስ ከርሞ በሞቃታማ ወቅት ደግሞ ሀገር ተነካ ሲባል ሕዝብ ሊጠበቅ ዘምቷልና፡፡ ይህ ጀግንነት በአንድ ጀንበር የመጣ አይደለም፡፡ ከዘር የቆዬ የሚታደሉት፣ ለእርሱ የተሰጠ ታላቅ ጥበብና ጀብድ ነው፡፡
ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ የኦሮሞና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ በሚለው መጻሕፋቸው ‹‹……ያለ አማሮች ወታደራዊ ድጋፍ ስርዎ መንግሥታት ገና ከመነሻቸውም በተንኮታኮቱ ነበር፡፡ ያ ብቻ አይደለም የኢትዮጵያ ነጻነት ሳይቀር አደጋ ላይ ይወድቅ ነበር፡፡ ለዚህ ተግባራቸው ኢትዮጵያዉያን በሙሉ የአማሮች ውለታ አለባቸው፡፡ አማሮች የኢትዮጵያ ነጻነት ጠባቂዎች ሆነው ባከናወኑት የመስዋዕት ተግባር ባንጻራዊ መልኩ ይበልጥ ጠንከር ያለ የኢትዮጵያዊነት ስሜት አዳብረዋል፡፡ ለዚህ ነው አማሮች ዘረኝነትን ከሚያራምዱ በተቃራኒው ከምንም ነገር በፊት ከአማራነትም በላይ ኢትዮጵያዊነት እጅግ ጎልቶ የሚበልጥባቸው፡፡ ……ለኢትዮጵያ ሀገርነት መኖር ሌሎች ኢትዮጵያዊያን የፈፀሙት ታላቅ ጀብዱ እንደተጠበቀ ሆኖ ስለ እውነት ብለን እውነት ብንናገር በኢትዮጵያ ነጻነት ላይ አማሮች የመሪነት ሚና ባይጫወቱ ኖሮ ቀኝ ገዢዋ ጣልያን ኢትዮጵያን በቀላሉ ድል አድርጋ ለመያዝ በቻለች ነበር፡፡ የዚህም ምስክሩ ጣልያን ናት፡፡ የአማራን ወሳኝ ሚና በመረዳቷ ከሁሉም በፊት አማራንና ተዋህዶ ሀይማኖትን ነበር ለማጥፋት የተነሳችው፡፡ አማሮች ከተበታተኑ ኢትዮጵያም እንደምትበታተን ጣልያኖች በሚገባ ያውቁ ነበር፡፡ ኢትዮጵያን አዳክመው ለመያዝ የሚሹ ከባሕር ማዶ የመጡም ሆነ የውስጥ ኃይሎች ሁሉ ይህንኑ አድርገዋል፡፡ የአማራ ጠላት የበዛውም ለዚሁ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ሌሎች ነጻነት ወዳድ ኢትዮጵያዊያን አገራቸውን ለመጠበቅ ያደረጉትን የጀግንነት ተጋድሎ ማሳነስ አይደለም›› በማለት ገልፀውታል፡፡
‹‹ ቆስቁሰው ቆስቁሰው ያቃጠሉት ክምር ብቻውን አይነድም ራሱን ሳይጨምር›› እንዳለ ከያኙ ትህነግ ያቀጣጠለው እሳት ራሱን በሚለበልበው ግንባር የተሰለፈው የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ጀብዱ እንዴት ይሆን? የአማራ ልዩ ኃይል አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር ቢሰጥ ጌታሁን ሕወሃቶች ለዓመታት ዝተውብናል፤ እነርሱ ለ30 ዓመታት በዘረፉትና ባከማቹት ትጥቅ ዝግጅት አድርገዋል፤ እንደነርሱ ረጅም ጊዜ ባይሆንም እኛም የክልሉ መንግሥት ባደረገልን ድጋፍ በቂ ዝግጅት አድርገን ነበር ሲሉ ቅድመ ውጊያውን ያስታውሱታል፡፡ የፀጥታ ኃይሉ ትህነግ ጥቃት ባደረሰችበት ምሽት በሚያስደንቅ መከላከልና መልሶ የማጥቃት ውጊያ ጥቃት የደረሰበትን የመከላከያ ሠራዊት መታደግ፣ መሳሪያዎችን ማስመለስና ወሳኝ የሚባሉ ቦታዎችን በመያዝ የቁርጥ ቀን መከታነቱን አሳይቷል ነው ያሉት፡፡
ውጊያው አቅማችን ያሳየንበት ነው ሲሉም አንስተውታል፡፡ የሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል እና የሚሊሻ አባላት በተሰለፉባቸው ግንባር አኩሪ ጀብዱ ፈፅሟል ያሉት አዛዡ ለተፈፀመው ገድል የመከላከያ ሰራዊት፣ ሚሊሻው፣ የመደበኛ ፖሊስ፣ የህዝቡና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ድርሻም የጎላ ነው ብለዋል፡፡ በተለይም ቅራቅር፣ ከተማ ንጉሥ፣ደጀና፣ ዳንሻ፣ ባዕከር፣ባናት፣ ማይካድራ፣ ልጉዲና ግራካሶ በተደረጉ ውጊያዎች ትህነግ ያመነችበትን የሰው ኃይልና መሳሪያ ተጠቅማ የተሰለፈችባቸው እንደነበር ያስታወሱት አዛዡ በውጊያው የሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል እና የሚሊሻ አባላት በሚያስደንቅ ጀብዱ ጠላትን በመደምሰስና በመማረክ ያሳዩት ብቃት ግሩም ነበር ነው ያሉት፡፡
በአውደ ውጊያው በህግ ተፈላጊ የነበሩ የጦር መኮንኖችንም መማረካቸውን ነው የተናገሩት፡፡ የሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ ልዩ ኃይሉና ሚሊሻው በቀጣይም በውጊያ ስነምግባራቸውና ጀብደኝነታቸው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡ ትህነግ ለዓመታት ለጦርነት ብትዘጋጅም የሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ተገፍቶ በገባበት ውጊያ ባሳዬው ቁርጠኝነት የዓመታት ድካማቸውን ከንቱ እንዳስቀረውም ተናግረዋል፡፡ የታዬው ልዩ ጀብድ የአባቶችን የጀግንነት ታሪክ ያስቀጠለ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የትህነግ የትጥቅ ብዛትና የዓመታት ዝግጅት በተደረጉ ውጊያዎች መና መሆናቸውን አስመስክረናልም ብለዋል፡፡ የሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ የክልሉ የፀጥታ ኃይልና የሚሊሻ አባላት ፍትኃዊ የሆነ ሥራ ነው የሠሩት፣ ከተለያዩ ቦታዎች ጫና ሊፈጠር ይችላል፣ የሰውን መብት አንነካም፣ ነገር ግን ወደኃላ አንመለስም፣ ታሪክ አድሰናል፣ ሁለተኛ ታሪክ አናበላሽም፤ ሕዝባችንን የመጠበቅ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡
የአማራ ክልል ከተስተካከለ ኢትዮጵያ ትስተካከላለች፤ ይህ ካልሆነ ግን ኢትዮጵያ አትስተካከልም ያሉት አዛዡ ለፌደራል መንግሥቱ የሚጠበቅብንን ድጋፍ በመስጠት እንቀጥላለንም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ