
“የህወሓት ጁንታ ንብረትነቱ የመከላከያ ሰራዊት ባልሆነ ሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ተፈጽሞብኛል የሚለው መረጃ ከእውነት የራቀ ነው” ሜጀር ጄኔራል ይልማ መርዳሳ
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 11/2013 ዓ.ም (አብመድ) ስግብግቡ የህወሃት ጁንታ ንብረትነቱ የመከላከያ ሰራዊት ባልሆነ ሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ተፈጽሞብኛል የሚለው መረጃ ከእውነት የራቀ መሆኑን የአየር ሀይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለፁ።
ሜጀር ጀኔራል ይልማ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የኢፌዴሪ አየር ሀይል የሀገርን ሉዓላዊነት እና የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ በሚያስችል ደረጃ ቴክኖሎጂ የታጠቀ መሆኑን አንስተዋል።
አየር ሀይሉ የሀገሪቱን አየር ክልል ከጥቃት በብቃት የመጠበቅ እና እንዳሁኑ ደግሞ የከረሩ ነገሮች ሲፈጠሩ ለሰራዊቱ የቅርብ ድጋፍ የማድረግ ተግባሩን እየተወጣ ይገኛልም ብለዋል።
የጠላት ኢላማዎችን ያለምንም ርህራሄ እንዳልነበር ማድረግ ለሰራዊቱ ማነቆ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን በማፍረስ መንገዱን ቀና የማድረግ ተግባር ይከውናልም ነው ያሉት፡፡
ሜጀር ጄኔራል ይልማ ከዚሁ ጋር በተያያዘ፤ ስግብግቡ የህወሓት ጁንታ ተቆጣጠርኩ ብሎት የነበረው መሳሪያ በማግስቱ በአየር ሀይሉ ወደ አመድነት ተቀይሯል ብለዋል።
ኃላፊነት በማይሰማው ቡድን በዱር በገደሉ የኮንትሮባንድን መንገድ ተከትሎ የደረሰው የጦር መሳሪያ እጣ ፈንታም ቢሆን በአብዛኛው ተመሳሰይ እድል ገጥሞታል ብለዋል።
በመቐለ አቅራቢያ ኪያ እና አዲግራት ጭምር የነበሩ የነዳጅ ዴፖዎችም በጁንታው ቡድን ጥቅም ላይ ሳይውሉ መውደማቸውን ተናግረዋል፡፡
እስካሁን የተዋጣላት ሀገርንም ያኮራ ስራ እና እርምጃ የተወሰደ ሲሆን፥ በዚህ ሁሉ ውስጥ ህገ ወጡ ቡድን የአየር ድብደባው ንጹሃንን እና የተለያዩ የእምነት ተቋማትን እንዲሁም የህዝብ መገልገያ ፕሮጀክቶችን ኢላማ ስለማድረጉ ክስ ያቀርባል።
የአየር ሀይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፥ ውንጀላው ከእውነት የራቀ መሆኑን እና ይህ የቡድኑ የኖረ የውሸት እና የውንብድና ትርክቶች መሆናቸውን አውስተዋል።
የጦር አውሮፕላን መትተን ጥለናል የሚለው የህገ ወጡ ቡድን የበሬ ወለደ ወሬ እንጂ የአቅም እና የመሳሪያ ሁኔታው አልፈቀደለትም ይላሉ ሜጀር ጄኔራል ይልማ መርዳሳ።
የትግራይ ወንድም እና እህቶችን ህይወት እና ሀብት ባላስገበረ መልኩ የተለዩ ኢላማዎችን የማጥቃት እርምጃው እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
“ይህን ስናደርግ ደግሞ በራሳችን በገነባነው የቴክኖሎጂ ልክ እንጂ የማንንም እርዳታ እና ድጋፍ አንጠይቅም” ብለዋል ሜጀር ጄኔራል ይልማ መርዳሳ።
ስግብግቡ ቡድን ሀገር እና ህዝብ ማለት ለርሱ እሱን እስከጠቀመ ብቻ መሆኑን በቅርብ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን ባወደመበት አይተናል ብለዋል።
ስለዚህ ዜጎች ይህን ቡድን ለመንቀል በሚደረገው ጥረት ተባባሪ ይሆኑ ዘንድም ጥሪ አቅርበዋል ፋብኮ እንደዘገበው።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a