
በመተከል ዞን የንጹኃን ዜጎችን ሕይወት የሚቀጥፉትን ፀረ ሰላም ኃይሎች እስከ መጨረሻው ለመደምሰስ እየተሰራ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 10/2013 ዓ.ም (አብመድ) በመተከል ዞን በሚደርሰው ተደጋጋሚ ግድያ ዜጎች ሕይዎታቸውን እያጡ ነው፡፡ ከቤት ንብረታቸው እየተፈናቀሉ ነው፤ በክልሉ ለዓመታት የቀጠለው ሞት አሁንም መቋጫ አልተገኘለትም፡፡ በአካባቢው በታጠቁ ኃይሎች የሚገደሉ ንፁሃን ዜጎች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ለመንግሥት አቤቱታ ቢያቀርቡም እስካሁን ድረስ ዘላቂ መፍትሔ የሰጣቸው አካል ግን አልተገኜም፡፡ በአካባቢው የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት እርምጃዎችን አጠናክሮ ቢወስድም ሰው በላዎቹ አሁንም በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚያደርሱትን ግድያ አላቆሙም፡፡
በመተከል ወቅታዊ ጉዳይ ከኢቲቪ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በመተከል ዞን ተደጋጋሚ ግድያ ይደርሳል ብለዋል፡፡ ባለፉት ጊዜያት የተከሰቱትን ችግሮች የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከአጎራባች ክልሎችና ከፌደራል መንግሥት በሚደረገው እገዛ ሽፍቶችንም ሆነ አስተባበሪዎችን ለሕግ እንዲቀርቡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በየደረጃው ባለው መዋቅር ኃላፊነት የማይወጡትንና በወረዳና በየቀበሌ የሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ኃይሎች ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጄት ወደ ህግ ለማቅረብ ተከታታይ የሆነ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል፡፡
በአካባቢው ያለው ሁኔታ በጣም ውስብስብ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግሥት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን አስታውቀዋል፡፡ በዞኑ በተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ከ100 በላይ ፀረ ሰላም ኃይሎች ተደምስሰዋልም ብለዋል፡፡ በየደረጃው ካለው የሥራ ኃላፊ፣ የፀጥታ ኃይልና ተባባሪ ግለሰቦችንም በቁጥጥር ስር አውለናል ብለዋል፡፡
በአካባቢው ያለው የፀረ ሰላም ኃይል ከትህነግ ጁንታና ከውጭ ሀገር ከሚኖሩ ጸረ ሰላም ኃይሎች ጋር ግንኙነት ያለው መሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ በቅርብ ጊዜም ሰላማዊ ዜጎችን ዘግናኝ በሆነ መንገድ ግድያ ፈጽሞባቸዋል ነው ያሉት፡፡
በመተከል ያለውን ችግር ለመቅረፍ የክልሉ መንግሥት ከፌደራል መንግሥት ጋር በመሆን በከፍተኛ ትኩረት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በጥቃቱ ለተፈናቀሉ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ እያደረጉ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a