
የአዳማ ከተማና የአዲስ አበባ ዙሪያ ነዋሪዎች በራያ ግንባር ለተሰለፉት ለሐገር መከላከያ፣ለአማራ ልዩ ኃይልና ለሚሊሻ አባላት ድጋፍ አደረጉ።
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 10/2013 ዓ.ም (አብመድ) ነዋሪዎቹ በትህነግ ዘራፊና ታጣቂ ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለውን የህግ ማስከበር እርምጃ በመደገፍ 176 የበሬ ሰንጋና 230 የፍየል ሙክቶችን ይዘው ራያ ቆቦ ተገኝተዋል።
የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ አባ ገዳዎች፣የሐገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ተገኝተው ለሐብት አሰባሳቢ ኮሚቴው ድጋፉን አስረክበዋል።
መንግስት የሐገር ሉዓላዊነትን በመዳፈር ክህደት የፈጸመውን የትህነግ ዘራፊ ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደግፋለን፤ ህግ አስከባሪ ሰራዊቱም እየወሰደ ባለው ታላቅ ጀብድ ኮርተናል ፤ ድጋፋችንንም አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል አባገዳዎችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች።
በራያ ግንባር ከፍተኛ አመራር ሌተናል ጀነራል ይመር መኮንን በበኩላቸው በራያ ግንባር የተሰለፈው ሰራዊት የትህነግ ጁንታ ያሰለፋቸውን ታጣቂ ኃይሎች በመደምሰስ ድል እየተቀዳጀ መሆኑን ተናግረዋል። ለተገኘው ድል የህዝቡ ሁለንተናዊ ድጋፍ ትልቅ አቅም እንደሆናቸውም አረጋግጠዋል።
“ምን የጦር ሰራዊት ቢኖር የህዝብ ድጋፍ ካላገኘ አሸናፊ መሆን አይቻልም ያሉት ሌተናል ጀነራል ይመር ድሉ የተመዘገበው ህዝባዊ አቅም በማግኘታችን ነው” ብለዋል።
በትህነግ ዘራፊና ከሐዲ ቡድን ላይ እርምጃ በመውሰድ የሐገር ክብርን ለማስጠበቅ ለተሰለፉት የመከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት ህዝቡ እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚደነቅ ነው ያሉት የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ወርቀሰሙ ማሞ የኦሮሚያ ክልል ህዝብ ድጋፍ በማድረጉ በክልሉ መንግስት ስም አመስግነዋል።
የትህነግ ጁንታ ለህግ እስኪቀርብ ድረስ ህዝቡ ለሰራዊቱ እያደረገ ያለውን ድጋፍም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- ስማቸው እሸቴ – ከራያ ግንባር