ባለፉት 15 ቀናት የሀገርን ሰላም ለማደፍረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 287 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፌዴራል ፖሊስ ገለጸ።

185
ባለፉት 15 ቀናት የሀገርን ሰላም ለማደፍረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 287 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፌዴራል ፖሊስ ገለጸ።
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 09/2013 ዓ.ም (አብመድ)
ባለፉት 15 ቀናት የፌዴራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባካሄዱት የተቀናጀ ኦፕሬሽን የሀገርን ሰላም ለማደፍረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 287 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል።
ከፅንፈኛው ሕወሓት እና ኦነግ ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብው የተጠረጠሩት 287 ግለሰቦች ከጦር መሳሪያዎች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን ነው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ያስታወቀው።
ፅንፈኛው የሕወሓት ቡድን በትግራይ ክልል በነበረው የሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት እና የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን ሲጠብቁ በነበሩ የፌዴራል ፓሊስ አባላት ላይ በፈፀመው ጥቃት ግድያ እና አፈና መፈፀሙን ኮሚሽኑ አስታውሷል።
ይህ ቡድን በመሀል ሀገርም ሊያደርስ የሚችለውን ማንኛውንም ጥቃት አስቀድሞ ለመከላከል ከቡድኑ ጋር ግንኙነት ያላቸውን አካላት ከእኩይ ተግባራቸው ለመግታት የፌዴራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖች ላለፉት 15 ቀናት ዘመቻ ሲያካሂዱ ቆይተዋል።
በዚህም አንዳንድ ድርጅቶች ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጭ ለሀገር እና ለህዝብ ስጋት የሆነ ተግባር ላይ መሰማራታቸው እንደተደረሰበት ነው ኮሚሽኑ ያብራረው።
ለአብነት ሱር ኮንስትራክሽን በተባለው ድርጅት ላይ በተደረገ ህጋዊ ብርበራና ፍተሻ ለተለያዩ ዘመቻዎች የተዘጋጁ ተሽከርካሪዎች፣ የፀሀይ ሀይል ማመንጫ፣ ተንቀሳቃሽ እና ቋሚ ወታደራዊ ሬዲዮ መገናኛዎች በህንፃው ምድር ቤት ተሸሽጎ እንዳለ መያዙን የፌዴራል ፓሊስ ኮሚሽን በመግለጫው አስታውቋል።
በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ከፅንፈኛው ሕወሓት እና ከኦነግ ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው ብሎ የጠረጠራቸውን 287 ሰዎች በቁጥጥር ስር አውሎ ምርምራ እየተካሄደባቸው ነው ተብሏል።
በከተማዋ በተደረገ ብርበራ፣ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ፣ በፖሊስ አሰሳ እና ከግለሰቦቹ እና ከተጠረጠሩ ተቋማት 1 ሺህ 32 የተለያዩ ጠመንጃዎች፣ 131 የተለያዩ ሽጉጦች እና 46 ሺህ 39 ጥይቶች ተይዘዋል።
እንዲሁም 14 ቦምቦች፣ 1 ፈንጂ፣ 5 ጂ ፒ ኤስ፣ 8 የጦር ሜዳ መነፀር፣ 5 ካቴና፣ 55 የክላሽ መጋዘን እና እጀታ፣ 1 ሺህ 339 የተለያዩ የኮሙኒኬሽን መሳሪያዎች፣ 845 ሺህ 434 የሀገር ውስጥ ገንዘብ እና 227 ሺህ 271 የተለያዩ የውጭ ሀገራት ገንዘቦች እንደተያዙ ነው ፓሊስ የገለፀው።
በተጨማሪም የተለያዩ የሰራዊት አልባሳት፣ ፓስፖርቶች፣ የውጭ ሀገር የስራ ፍቃድ ሰነዶች፣ በርካታ ገንዘብ ያዙ የባንክ ደብተሮች ፣ በሽጉጥ ላይ የሚገጠም የድምፅ ማፈኛ፣ የተለያዩ ኮምፒዩተሮች፣ ፀረ ታንክ መሳሪ እና ሌሎች መሳሪያዎች መያዛቸውም ተጠቁሟል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ከሚገኘው ዘመቻ ጋር ተያይዞ የጥፋት ሀይሉ ተላላኪዎች ሊጠቀሙባቸው የነበሩ የጦር መሳሪያዎች ሆን ብለው ዜጎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ በሚችል መልኩ በየቦታው ጥለዋቸው የነበረ ቢሆንም ፓሊስ ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ሊያከሽፋቸው እንደቻለ ኢብኮ ዘግቧል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበምዕራብ ወለጋ ዞን በ142 የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ፡፡
Next articleየአዳማ ከተማና የአዲስ አበባ ዙሪያ ነዋሪዎች በራያ ግንባር ለተሰለፉት ለሐገር መከላከያ፣ለአማራ ልዩ ኃይልና ለሚሊሻ አባላት ድጋፍ አደረጉ።የአዳማ ከተማና የአዲስ አበባ ዙሪያ ነዋሪዎች በራያ ግንባር ለተሰለፉት ለሐገር መከላከያ፣ለአማራ ልዩ ኃይልና ለሚሊሻ አባላት ድጋፍ አደረጉ።