
80 በመቶ የጣና ሐይቅ የእምቦጭ አረም ተነቅሏል፡፡
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 09/2013 ዓ.ም (አብመድ) ከጥቅምት 9 እስከ ኅዳር 9/2013 ዓ.ም በጣና ሐይቅ የተስፋፋውን እንቦጭ ለማስወገድ ሀገራዊ ዘመቻ መጀመሩ ይታወሳል፡፡ የጣና ሐይቅና ሌሎች ውሃማ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጄንሲ ሥራ አስኪያጅ አያሌው ወንዴ (ዶክተር) ለአንድ ወር በቆዬው ዘመቻም ባሉት ሀያ የሥራ ቀናት ወደ ስራ ሲገባ ከነበረው 4 ሺህ 300 ሄክታር መሬት 80 በመቶው የሚሆነውን የእንቦጭ አረም ማስወገድና ማከማቸት ተችሏል ብለዋል፡፡
ዘመቻው አሥር የሥራ ቀናት እንደሚቀሩት የተናገሩት ዶክተር አያሌው ቀሪ ሥራዎች በትጋት ይሠራሉ ነው ያሉት፡፡ ሕዳር 20 /2013 ዓ.ም የዘመቻው የመዝጊያ ሥነ ስርዓት እንደሚደረግም ገልፀዋል፡፡ 80 በመቶው የተነቀለውንና የተከማቸውን የእንቦጭ አረም መነስነስ፣ መልቀምና ማቃጠል እንደሚቀርም ተናግረዋል፡፡
ወደ ዘመቻ ሲገባ 90 በመቶውን የእንቦጭ አረም ለማስወገድ ዕቅድ መያዙን የተናገሩት ዶክተር አያሌው በቀሪ ቀናት ከዕቅዱ በላይ ሊሠራ እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡ የእንቦጭ አረም ባልተነቀለባቸው ቀበሌዎች በቀሪ አሥር የሥራ ቀናት በሙሉ የሠው ኃይል እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
በዘመቻው በሠው ኃይል ብቻ ሳይሆን ማሽኖችም አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ዶክተር አያሌው ተናግረዋል፡፡ ሁለት ቀበሌዎች ውሃው ጥልቀት ስላለው ለሌላ ጊዜ መሸጋገራቸውንም ተናግረዋል፡፡
በ20 የሥራ ቀናት 260 ሺህ ዜጎች በዘመቻው መሳተፋቸውንም ተናግረዋል፡፡ በዘመቻው በቀን ከ2 ሺህ እስከ 14 ሺህ ዘማቾች እንደተሳተፉም አብራርተዋል፡፡ በተገኘው ውጤት ማኅበረሰቡ ለቀጣይ ስራ መነሳሳቱንም ገልፀዋል፡፡ የይቻላል መንፈሱም ትልቁ የዘመቻው ግብ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
እንቦጭን በሰው ጉልበት ከኢትዮጵያ ውጭ በየትኛውም ዓለም ያስወገደ ሀገር አለመኖሩን የተናገሩት ዶክተር አያሌው ”በሠው ጉልበት ታሪክ ሰርተን አሳይተናል፤ ታሪክም እንሰራለን“ ብለዋል።
ለተገኘው ውጤት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ በዘመቻው እስከሚሰለፍው ህብረተሰብ ድረስ የነበረው ቅንጅታዊ አሠራር ውጤታም እንደነበርም ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡ በዘመቻው የተገኘው ውጤት እንቦጭን ሙሉ ለሙሉ ተወግዷል ማለት እንዳልሆነና ቀጣይ ከባድ ሥራዎች እንዳሉም አስገንዝበዋል፡፡
አረሙ ላለፉት ዓመታት በሐይቁ ላይ ዘሩን ስለጣለ የማይቋረጥ ክትትል ያስፈልገዋል፤ አካባቢውን በነባር ዕፅዋት መተካትና ልቅ ግጦሽን መከላከል እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል፡፡
በቀጣይ እንቦጭን የማፅዳት ሥራ ማኅበረሰቡ ተደራጅቶ እንዲመጣ ጥሪ ያቀረቡት ዶክተር አያሌው በቅንጅት ከተሰራ የቀረውን አረም በቀላሉ ማስወገድ ይቻላልም ብለዋል፡፡
ለዘመቻው የገንዝብ ድጋፍ የሚያደርጉና ገንዘቡን ያልከፈሉ የክልልና የፌዴራል ተቋማት ገንዘቡን እንዲከፍሉም ጠይቀዋል፡፡ ሁሉም በጥንክሬ በመሥራት ድርብ ድል ማስመዝገብ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ