
“አይረጋጉም፣ አደገኛ ናቸው፤ አስፈሪ ናቸው፤ የተባሉ የጦር ቀጣናዎችን በብቃት አረጋግቷቸዋል”
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 08/2013 ዓ.ም (አብመድ) በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በወቅቱ ምደባ በእጣ ነበርና የቀጣይ የመምህርነት ሕይዎታቸው መከላከያ ሚኒስቴር ሆነ፡፡ ሠራዊቱ ባለበት የሀገሪቱ አካባቢዎች ሁሉ እየተዟዟሩ የቀለም ትምህርት አስተምረዋል፡፡
ሠራዊቱ ያረፈባቸው፣ ያካለላቸውና የተጓዘባቸው አካባቢዎች ሁሉ አብረው አሉ፤ ለ17 ዓመታትም አገልግለዋል፣ አቶ አብረሃም ግርማይ፡፡ ምንም እንኳን አሁን ላይ የሥራ ዘርፍ ቀይረው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እየሰሩ ቢሆንም በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ስለነበራቸው ጥዑም የሥራ ዘመን አውርተው አይጠግቡም፡፡
ሥለ ሰሞኑ በትህነግ ከሀዲ ቡድን በሰሜን እዝ ላይ ስለፈጸመው ክህደት እና ስለ ኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጀብድ በተመለከተ በስልክ ሲናገሩ የእንባ ሳግ ሲተናነቃቸው ከድምጻቸው በግልጽ ይታወቅ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን የክህሎት፣ የእውቀት እና የአመለካከት ብቃት ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ አቶ አብረሃም “ወታደር ባልሆንም እንደ አንድ ብዙ ዓመታትን አብሮ እንደሠራ ሰው መከላከያ ሰራዊታችን በደንብ ነው የማውቀው” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የጀግንነት ታሪኩ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የወጣ መሆኑ፣ ለሀገር ያለውን ጥልቅ ፍቅር፣ በተሰማራባቸው የጦር አውዶች የፈጸማቸውን ጀብዶች፣ አዲስ ነገር ለማወቅ ያለውን ጥልቅ ፍላጎትና ሌሎች ጥንካሬዎቹንም ጠቅሰዋል፡፡
እንደ አቶ አብረሃም ግርማይ ማብራሪያ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በተቀረው ዓለም ጭምር መልካም የሚባል ሥም አለው፡፡
በሠላም አስከባሪነት በተሰማራባቸው የውጭ ሀገራት ጭምር በጀግንነት፣ በወታደራዊ ጥብቅ ዲሲፕሊን እና በሰብአዊነት ግዳጁን በሚፈለገው ልክ ስለሚወጣ በሕዝቡ ክብር የሚሰጠው መሆኑን አብረው በተጓዙባቸው ጊዜአት ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል፡፡
“አይረጋጉም፤ አደገኛ ናቸው፤ አስፈሪ ናቸው፤ የተባሉ የጦር ቀጣናዎችን ጭምር የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በብቃት አረጋግቷቸዋል፤ የላይቤሪያ የእርስ በርስ ጦርነት የኢትዮጵ መከላከያ ሠራዊት ሲገባ ነው የተረጋጋው፤ ከዚያ በፊት ሌሎቹ ሞክረው አልተሳካላቸውም፤ ጀግና እና ዓለም የሚያደንቀው ሠራዊት ነው” ሲሉ እርሳቸው አብረው የተሳተፉበትን እና የተመለከቱትን ለአብነት አንስተዋል፡፡
በቡሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ ሱዳን ዳርፉር፣ አብዬ፣ ላይቤሪያና ሶማሊያ ያስመዘገባቸውን ደማቅ ዓለም አቀፋዊ ጀብዶች ጠቅሰዋል። አልሸባብን እና መሰል የሀገርን ብሎም የቀጣናውን ጠላት መደምሰስ፣ ዜጎችን ከጥቃት መከላከል፣ የአካባቢው ሠላም እንዲረጋገጥ የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣቱን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ስንቁን እያካፈለ ብዙዎችን መግቧል፤ ለሕይዎቱ ሳይሳሳ፣ ለጉልበቱ ሳይሰስት ኅብረተሰቡን አገልግሏል፤ ከደሞዙ በመቀነስ ትምህርት ቤት እና መሰል የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ገንብቷል፤ ይሄን አቶ አብረሃም ሠራዊቱ በ1996 ዓ.ም በላይቤሪያ ሠላም ለማስከበር በተባበሩት መንግስታት ጥላ ስር በተሰማራበት ግዳጅ ወቅት አብረው ተጉዘው ተመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያዊነት ፍቅር በሕዝቡ ልብ ውስጥ እንዲሰርጽ በመስራቱ ከሌሎቹ ሀገራት ሠላም አስከባሪ ሠራዊት በተለየ ሁኔታ በላይቤሪያ ሕዝብ ዘንድ ክብር እና ተቀባይነት እንደነረበውም ህያው ምስክር ሆነዋል፡፡
“እኔ ሠራዊቱን የምገልጽበት ቃላት ያጥረኛል፤ ሰው አክባሪ፣ ለአንተ ምቾትና ክብር እጅግ አብዝቶ የሚጨነቅ፣ ከሁሉም ነገር አስቀድሞ ለአንተ የሚሳሳ ሠራዊት ነው” ሲሉ ገልጸውታል አቶ አብረሃም፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሀገሩ የሰጠቸውን አደራ በብቃት የሚወጣ፣ ብቃት ያለው፣ ክብር ሚገባው ሠራዊት እንደንደሆነም አስረድተዋል፡፡
በትህነግ ከሀዲ ቡድን የተፈጸመው ክህደት አሳፋሪ እና አሳዛኝ እንደሆነና በራሱ ጓዶች ተከድቶ እንደገና ራሱን አደራጅቶ ከሀዲውን ቡድን ወደ መደምሰስ መሸጋገሩ ምን ያህል የላቀ ብቃት ያለው ሠራዊት መሆኑን እንደሚያሳይ ነው አቶ አብረሃም ተናግረዋል፡፡
በተፈጸመበት ክህደት በቁጭት እና በጀግንነት የትህነግን ጁንታ ቡድን እየደመሰሰ ወርቃማ ድሎችን እያስመዘገበ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ “ሠራዊቱ ወደ እንደዚህ አይነት ድል መሸጋገሩ ብቃቱ የቱን ያህል የላቀ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፤ እጅግ በጣም እንድትኮራበት የሚያደርግህ ሠራዊት ነው፤” ብለዋል።
አቶ አብረሃም በቀጣይም መከላከያ ሠራዊቱ ኢትዮጵያን የሚያኮራ ሥራ እንደሚሠራ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ ክብር ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት!
ዘጋቢ፡- የማነብርሃን ጌታቸው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ