የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ለትህነግ ቡድን የዲፕሎማሲ ሥራ እየሰሩ ነው ተባለ፡፡

415
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ለትህነግ ቡድን የዲፕሎማሲ ሥራ እየሰሩ ነው ተባለ፡፡
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 08/2013 ዓ.ም (አብመድ) የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከድርጅቱ መርህ ውጭ ለትህነግ ጁንታ ቡድን ወታደራዊ ድጋፍ በማፈላለግ እየተላላኩ መሆኑን የቱርክ አናዶሉ የዜና ወኪል ዘግቧል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ በብዙ የዓለም ክፍሎች ደጅ በመጥናት ለትህነግ የዲፕሎማሲ እና ወታደራዊ ድጋፍ በመጠየቅ ላይ ሙሉ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውንም ዘገባው ጠቅሷል፡፡
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2017 ጀምሮ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው እየሠሩ ያሉት ዶክተር ቴዎድሮስ የትህነግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እንደነበሩም አስታውሷል፡፡
በተጨማሪም እ.ኤ.አ ከ2005 እስከ 2012 የኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር እና እ.ኤ.አ ከ2012 እስከ 2016 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደነበሩ አውስቷል፡፡
አንድ የሀገሪቱን ከፍተኛ ባለስልጣን ጠቅሶ አናዶሉ እንደዘገበው በትህነግ ቡድን ላይ የሕግ ማስከበር ዘመቻ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የኢትዮጵያ መንግሥት የዶክተር ቴዎድሮስ እንቅስቃሴ በተመለከተ በሚገባ መረጃ አለው፡፡
ዶክተር ቴዎድሮስ የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶችን የፌዴራል መንግስት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በትህነግ ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን ወታደራዊ እርምጃ እንዲያስቆሙ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና ለማሳደር ሲጠይቁ ነበር ተብሏል፡፡
ዶክተር ቴዎድሮስ መንግስት እየወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር ዘመቻ እያጣጠሉ እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡
ግብፅ ለትህነግ ቡድን ወታደራዊ ድጋፍ እንድታደርግ ጭምር መጠየቃቸውንም ባለስልጣኑ ለአናዶሉ ጠቅሰዋል፡፡
ባለስልጣኑ ቴዎድሮስ አድሃኖም (ዶክተር) ለአስርት ዓመታት ኢትዮጵያን በማተራመስ እና የታላቁን ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል ከቆመችው ግብፅ ጋር መመሳጠራቸው የሀገር ክህደት ነው ሲሉ መግለጻቸውን ዘገባው ጠቅሷል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ በሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራትም ለትህነግ ቡድን ጥብቅና በመቆም እና ድጋፍ እንዲሰጡት እየወተወቱ ነው ተብሏል፡፡ ለዚህም የበርካታ የጎረቤት ሀገራትን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ደጋግመው በመጥራት ለትህነግ ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጫና እየፈጠሩ እንደሆነ ሀገራቱ ለኢትዮጵያ መንግስት አሳውቀዋል ተብሏል፡፡
ሀገራቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ህግ የማስከበር ሥራ እየሠራ መሆኑንና ጉዳዩ ውስጣዊ በመሆኑ የዶክተር ቴዎድሮስን ጥያቄ ውድቅ እንዳደረጉባቸው መረጃ ወጥቷል፤ ይህ ብቻ ሳይሆን ሀገራቱ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን በመቆም ህግ የማስከበሩን ሂደት እንደሚደግፉም ተጠቅሷል፡፡
የአናዶሉ መረጃ ምንጭ የሆኑት ከፍተኛ ባለሥልጣን ዶክተር ቴዎድሮስ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሥራ በማይመለከት ጉዳይ እና የድርጅቱን መርህ በመጣስ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በየማብርሃን ጌታቸው
Previous article‹‹ እነርሱ ዘላለም እኛ ደግሞ ሁለት ደቂቃ ቆመናል››
Next articleየአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ በትግራይ ክልልና አዋሳኝ አካባቢችዎች ቁጥጥር እንደሚያካሂድ ገለጸ።