‹‹ እነርሱ ዘላለም እኛ ደግሞ ሁለት ደቂቃ ቆመናል››

271
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 08/2013 ዓ.ም (አብመድ) እነርሱ አይተኙም፣ የግል ሕይወት አይመኙም፣ ደስታቸውና ስኬታቸው ኢትዮጵያን አለማስደፈር ነው፡፡ ድንጋይ ተንተርሰው፣ ዳዋ ለብሰው፣ አንድ ኮዳ ውሃ ተቃምሰው፣ አልመው ተኩሰው ሀገርን ይጠብቃሉ፣ ወገንን ያኮራሉ፡፡ ስለሀገር አይተኙም፣ እነርሱ ሀገርንና ሕዝብን በማስቀደም ዘላለም ይቆሙልናል፡፡ ከሰማዩ ጠባቂ በመቀጠል በምድር የሚጠብቁን እነርሱ ናቸው፡፡ ከእነርሱ ውጭ መመኪያም መከታም የለንም፡፡
እነዚህን የሀገር መከታዎች ጠላት በተዳጋጋሚ ሞክሯቸው ሁሉም በሽንፈት ተመልሷል፡፡ በውስጥ ጠላት ግን ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ ምንም እንኳን ባጎረሰ ቢነከስም፣ ጠላቱን ለመደምሰስ ተጋድሎ ላይ ነው፡፡ በመከላከያው መነካት የተበሳጩት ኢትዮጵያዊያንም ጠላትን ለመደምሰስ በሚያደርገው ዘመቻ ደስተኞች መሆናቸውን እየገለፁ ነው፡፡ ጥንትም ማሸነፍ ማንነቱ የሆነው ወታደር የቆመለት ሕዝብ ድጋፍ ብርታት ሰጥቶት በየቀኑ አዳዲስ ድል እያስመዘገበ ነው፡፡
የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻም ጠላትን ከመመከት አንስቶ እስከማጥቃት ድረስ ድል በድል እየሆነ ነው፡፡
የሀገር መከላከያ ሠራዊቱን ጀብዱ በማድነቅ፣ በጀግንነቱ በመደነቅ ክብር ለመስጠት ሕዳር 8 ቀን 2013 ዓ.ም እርሱን የሚያስብ ዘመቻ እየተካሄደ ነው፡፡ ለመሆኑ የዚህ ጀግና ሠራዊት አይሸናፌነትና ጀብዱ ምን ይመስላል?
በባሕርዳር ዪኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ፋንታሁን አየለ (ዶክተር) የኢትዮጵያን ሠራዊት በዘመናዊ መንግድ ለማቋቋም የታሰበው በ1920ዎቹ ነበር፡፡ ነገር ግን በ1928 ዓ.ም ጣልያን ኢትዮጵያን በመውረሯ ዕቅዱ ተጨናገፈ ነው ያሉት፡፡ ምንም እንኳን በዘመናዊ መንገድ የመቋቋም ዕቅዱ ቢጨናገፍም የኢትዮጵያ አርበኞች በአምስት ዓመቱ የአርበኝነት ተጋድሎ በጀግንነት ሀገራቸውን ነጻ አውጥተዋል፡፡ ቅድመ ወረራ ታቅዶ የነበረው ሠራዊቱን በዘመናዊ መንገድ የማቋቋም ዕቅድ ከድል በኃላ ተሳክቶ ሠራዊቱ ተቋቋመ ነው ያሉት ዶክተር ፋንታሁን፡፡
ሠራዊቱ የሀገሩን ዳር ድንበር ከማስከበር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጀግንነቱንና አይበገሬነቱን አስመስከሯል ነው ያሉት፡፡ ለአብነትም እ.አ.አ ከ1950 እስከ 1953 በተካሄደው የኮሪያ ጦርነት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ኃይል ጋር በመዝመት አይሸነፌነትና አይበገሬነትም አስመስክሯልም ብለዋል ዶክተር ፋንታሁን፡፡ በኮሪያ ጦርነት አንድም ወታደር በጠላት ያልተማረከ ብቸኛው ወታደር የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ወታደር እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
እ.አ.አ በ1960 በኮንጎ በተነሳው ሁከት የኢትዮጵያ ሠራዊት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ኃይል ጋር በመዝመት ጀግንነቱን ማሳየቱንም አስታውሰዋል፡፡ በ1956 እና በ1969 ዓ.ም የሶማሊያ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ባካሄደበት ጊዜ ወራሪውን ድባቅ በመምታት የሀገሩን ዳር ድንብር አስከብሯል ነው ያሉት፡፡
‹‹ሳይደርሱባቸው እየደረሱ ይመለሳሉ እየቀመሱ›› እንዲሉ የትህነግ ከሃዲዎች የመከላከያ ሠራዊት አባላትን ከተነኮሱ በኃላ እየደረሰባቸው ያለውን ጥቃት አልቋቋም ሲሉ መከላከያ ሠራዊት ታሪካዊ ስህተት ፈፅሟል ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ዶክተር ፋንታሁን በዚህ ጉዳይ ‹‹ የትህነግ አባላት የሚነግሩን ተቃራኒውን ነው፤ ታሪካዊ ስህተት የፈፀመው መከላከያ ሠራዊት ሳይሆን ትህነግ ነው፤ ትህነግ የራሱን ሀገር መከላከያ ሠራዊት ፍፁም ባላሰበው መንገድ ማጥቃት ታሪካዊ ስህተት ከመፈፀምም በላይ የሀገር ክህደት ወንጀል ፈጽሟል>> ነው ያሉት፡፡
ሕወሃት በሀገራቸው የሚኮሩና ታሪካቸውን የሚወዱ ዜጎችን እንደጠላት ነው የሚያዬው ያሉት ዶክተር ፋንታሁን በተማሪዎች ንቅናቄ በተጀመረው የተሳሳተ ትርክት ሕወሃት አማራውን እንደጨቋኝ በመቁጠር በአማራ ተወላጆች ላይ ዘግናኝ ግፍ ሲፈፅምና ሲያስፈፅም ኖሯልም ብለዋል፡፡ በረጅም የመንግሥት መሥረታ ታሪክ ከአንድ ብሔር ብቻ የወጣ የገዥ መደብ አልታዬምም ብለዋል፡፡ በረጅም ዘመን ታሪኩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲጋባና ሲዋለድ መኖሩንም ገልፀዋል፡፡ በዚህ ሂደት ኢትዮጵያዊያን እርስ በእርስ መጋመዳቸውንና መዋሃዳቸውንም ተናግረዋል፡፡
ሕወሃት ግን የኢትዮጵያን እውነታ በመካድ ባለፉት ዓመታት የሀሰት ትርክቱን ሲለፍ ኖሯል ብለዋል፡፡ ለ27 ዓመታት አማራውን በተመለከተ የተሰራጨው የሀሰት ትርክት በየአካባቢው በግፍ እንዲገደልና እንዲጨፈጨፍ እያደረገው ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡
የሕወሃት የተሳሳተ ትርክት ለሀገር ግንባታ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን የገለፁት የታሪክ ምሁሩ እውነተኛውን ታሪክ ማስተማር ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
ስለ ምናከብራቸው እንቆምላቸዋለን፡፡ ስለሚወዱን እንወዳቸዋለን፡፡ ስለሚጠብቁን እንመከባቸዋለን፡፡ ለዘላለም ለሚቆሙልን እኛ ለደቂቃዎች እንቆምላቸዋለን፡፡ ከውድ ሕይወታቸው በላይ ሀገርንና ሕዝብን ያስቀድማሉና፡፡
ዘጋቢ፡-ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article‹‹ ስለማይችሉን አይወዱንም››
Next articleየዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ለትህነግ ቡድን የዲፕሎማሲ ሥራ እየሰሩ ነው ተባለ፡፡