ይብላኝ ለከሃዲው እንጂ ኢትዮጵያስ ከፍ ትላለች !!!

261
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 07/2013 ዓ.ም (አብመድ) አርግዞ መውለድ እንጂ አሳድጎ ለቁም ነገር ማብቃት አልታደለችም፡፡ የደከመውን ጉልበቷን ይደግፋሉ ተብሎ ሲታሰብ በለጋ እድሜያቸው የጥይት ሲሳይ ሆነው ይቀራሉ፡፡ ጥጋበኞቹ በቅንጡ ቤት ውስኪ ያንቆረቁራሉ፣ ሲያሻቸው ወጣ ብለው ማነው ወንዱ ብለው ይፎክራሉ፡፡ በግንባር ያሉት ታዳጊ ወጣቶች ግን ሳይገባቸው ያለእድሜያቸው ይቀጠፋሉ፡፡
ይብላኝ ለዚያች እናት ሀቋን ለተቀማች፣ ወልዳ ላልተጠቀመች፣ ወልዳ እያለቀስች ለኖረችው፡፡ የትግራይ እናት እውነቷ በህወሃት የተቀማባት፣ መቅኔዋ በችግር የደቀቀባት ናት፡፡ ሳትሰስት የምታጎርሰው እናት ኢትዮጵያ በውሰጧ ላትጠፋ ተቀርፃለች፡፡ የትህነግ እብሪተኝነትና የትግራይ እናት ማንነት ፈፅሞ አይገናኝም፡፡ ከኢትዮጵያ የሚነጥላትን ከኢትዮጵያዊነት ክብር ዝቅ የሚያደርጋትን ነገር ፈፅሞ አታደርግም፡፡
የትህነግን የሀገር ክህደት አሉላ አባ ነጋ ቢሰማ ምን ይል ይሆን? በኢትዮጵያ የመጣን ጠላት ተመለስ በሉት አይቀጡ ቅጣት ቀጥቼ እመልሰዋለሁ እያለ ጠላቱን ጉንደትና ጉራዕ ላይ እንዳልነበር ያደረገው ያ ጀግና እርሱ በተወለደባት ምድር ሀገርን የሚክድ ባንዳ ሲፈጠር ቢሰማ መሬት ባልበቃው ነበር፡፡ የሀገሩን መከታ ለመገርሰስ የጣረውን ቢያዬው እንዴት ባፈረባቸው፤ እንዴትስ አድርጎ አይቀጡ ቅጣት በቀጣቸው ነበር፡፡ በእርግጥ አሁንም በጀግና ኢትዮጵያዊያን አይቀጡ ቅጣት እየተቀጡ ነው፡፡
የትግራይ ሕዝብ በፅዮን ማርያም የሚያስቀድስ፣ በአቡነ አረጋዊ ታቦት የሚያነግስ፣ በነጋሺ መስጂድ ሶላት የሚያደርስ፣ ‹‹ሀፍተይ፣ሃወይ›› እህቴና ወንድሜ እያለ በመልካም ልብ አንጀትን የሚያርስ፣ ካለው ከፍሎ የሚያጎርስ፣ ለሀገር አንድነት የሚቆም ነው፡፡
‹‹አድዋና ሽሬ ተንቤንና እንደርታ፣ ውቅሮና አዲግራት አክሱም ፅዮን ማርያም ትግራይ ላይ ተወልዶ፤ ጠላት የሚመልስ ከባሕሩ ማዶ፤›› እየተባለ የተገጠለመት እንጂ የሀገሩን በር ሰብሮ ጠላት ግቡ የሚል አይደለም፡፡ ምን አልባትም አሁን ላይ በዘመነ ፍጻሜያቸው ላይ ያሉት የትህነግ አባላት የትግራይን ስነልቦና እና ሀገር ወዳድነት አያውቁትም፡፡ ቢያውቁት እንደዚህ ባላፈኑትና ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር እንዲለያይ ባልተፍጨረጨሩ ነበር፡፡ ዳሩ ለሺህ ዓመታት የዘለቀን ሀገር ወዳድነትና ፅኑ ኢትዮጵያዊነት በአራት አስርት ዓመታት መናድና ማውረድ አልቻሉም፡፡ ለማውረድ ባሰቡት መንገድ እራሳቸው እየወረዱ ነው፡፡
ሀገር የካዱ፣ ወንድምን ከጀርባው በጦር የወጉ፣ ሀገርን ለማፍረስ የጓጉ ጥቅመኞች በሰሜን እዝ ሀገር መካላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ፈፅመዋል፡፡
ሁሉ በአመነው እና የክፉ ቀን ባለው ጓደኛው የተከዳ አንድ አርሶ አደር ‹‹ኧረ ወንዛ ወንዙን ወንዙን አትመነው፤ አብሮት ያደገውን ዶቅማውን ነቀለው›› ሲል ተቀኘ፡፡ ትህነግም እንደወንዙ ሁሉ አብሮት ያደገውንና የኖረውን የሀገር መከታ ነው የወጋው፡፡ ከዚህ በኃላ ትህነግ በኢትዮጵያ ምድር እንዳይታመን ሆኖ ከሰውነት ወርዷል፡፡ ምንም ቢል የሚያምነው፣ ምንም ቢሆን የሚያዝነለት የለም፡፡ ይልቁንስ አሳዶ ይዞ እራሱ ወደሰራው የስቃይ ቦታ ይልከዋል እንጂ፡፡
‹‹ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱን ሊቀይር ይቻለዋልን?›› እንዳለ መጻህፍ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በኢትዮጵያዊነቱ ከመጣህበት የመጨረሻውን የፀብ ዱላ ያነሳብኃል፡፡ ባነሳው ዱላ የኢትዮጵያዊነትን ታላቅነት ያሳይኃል፡፡
ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ የኦሮሞና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ በሚለው መጻሕፋቸው
‹‹ ኢትዮጵያዊነቴን እወደዋለሁ፡፡ ምክንያቱም አያት ቅድመ አያቶቼ በዓለም መድረክ ላይ የተጫወቱት ሚና ያኮራኛል፡፡ አያት ቅድመ አያቶቼ ልዩ የሆነውን ቅርሳቸውን የተውልን የኢትዮጵያን ዳር ድንበር አስከብረው መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ጠቅላላ ኢትዮጵያ በሙሉ ቁመቷና ስፋቷ የእኔና የሌሎችም ኢትዮጵያዉያን ናት፡፡ እርሷን ለማትረፍና ለእኛ ለማስተላለፍ ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰዋልና፡፡ በሕዝቦቿ ቅርፅ መልክና፣ በቋንቋዎቿ ብርቅነት፣ በሙዚቃዋ ጥልቀት፣ በጭፈረዋ አማላይነት፣ በስነ ቃሏ፣ በታሪኳ፣በፍልስፍናዋና በስነፅሑፏ እማረካለሁ፡፡ በሃይማኖቷ፣ በዜጎቿ መልካም ጠባይ፣ በጨዋነታቸው፣ ለሕይወት ባለቸው አመለካካት፣ በአዕምሯቸው ረቂቅነትና ጥልቀት እሳባለሁ፡፡ በክብራቸው አስፈሪነት፣ በንግግራቸው ተራቃቂነት፣ በጥበባቸው ውስብስብነት፣ በአለው ኩራታቸው ጥልቀትና ተወዳዳሪ በማይገኝለት ገርነታቸው በጥቅሉ ለመላው ብዙሕነታቸው እሸነፋለሁ›› ይሏታል፡፡
ኢትዮጵያዉያን በአረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሰንደቅ የገቡትን ቃል ኪዳን አያጥፉትም፡፡ በሀገር የገቡት ቃል ከሚያልፍ ሕይታወታቸው ቢያልፍ ደስታቸው ነው፡፡ ለዚያም ነው ኢትዮጵያ ተነካች ሲባሉ ቀፎው እንደተነካበት ንብ በህብር የሚነሱት፡፡ አካኪ ዘራፍ ብለው ቃታ ከሳቡ በፊታቸው የሚበረክት ጠላት አይገኝም፡፡ እንደ ጨርቅ እየተቀደደ፣ እንደ አረጀ ዛፍ እየወደቀ፣ ወደኋላ እያፈገፈገ የመጣበት የሀገሩ ድሃና (አቅጣጫ) እስኪጠፋበት ድረስ መውጫ መግቢያ ያጣል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ክብራቸውን የነካ ከክብሩ ያወርዱታል፣ ሰንደቃቸውን የነካውን ይቀጡታል፤ በሉዓላዊነታቸው እጁን የዘረጋውን ሁሉ እጁን ያሳጥሩታል፤ የሰንደቃቸው ቃል ኪዳን በጭንቅ ጊዜ ላይፈታ፣ በጠላት ግንባር ላይረታ፣ ከምድር ከፍታ ሁሉ ከፍ ብሎ የተሰቀለ ለዘላለም ፀንቶ የሚኖር ነው፡፡
ትህነግ በፈጸመው የሃገር ክህደት እየተወሰደበት ባለው ህግ የማስከበር የህልውና ዘመቻ በጣዕረ ሞት ላይ እንዲገኝ አድርጎታል፡፡
ለጊዜ ክብር ይግባውና ትህነግ የማይቻለውን ተራራ ገጭቶ ተምዘግዝጎ እየወደቀ ነው፡፡ ለዓመታት በግፍ የሞቱ፣ የተሰቃዩና በአረንቋ ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ትህነግ በማይመጣው ሲመጣባቸው አሻፈረኝ ብለው ተነሱበት፡፡
አሁን ከፊሉ ዘማች፣ ከፊሉ አዝማች፣ ከፊሉ ስንቅ አቀባይ ሆኖ የቀረበው በጥይት፤ የራቀው ደግሞ በድጋፉ የኃላ ደጀን ሆኖ ትህነግን እየቀጡት ይገኛሉ፡፡ በዚህ ወቅት የተነኩት እየወጉት፣ ያላመኑት እየከዱት፣ በስህተት የቀረቡት እየራቁት እድል ሁሉ ከእርሱ እየራቀበት ነው፡፡ ለእርሱ ብርሃን ለኢትዮጵያውያን ጨለማ የነበረው ዘመን እያከተመ ይመስላል፡፡
የትህነግ ግፈኞች ጨለማ ሊያዩ ቀርበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብርሃን ሲገለጥ የትግራይ እናት እውነትም አብሮ ይገለጣል፡፡ ለትግራይ ሕዝብ የቆምኩለት ነኝ እያለ የሚያላዝነው ሕወሃት የትግራይ ሕዝብ እንዳይራመድ ከመንገዱ ላይ የቆመበት መሆኑ በቅርብ የሚታይ ይመስላል፡፡ ያን ጊዜ በሌለ ቤቷ ወልዳ የምታሳድግ እናት የእሳት እራት ሳይሆን የዘመን መብራት የሆነ ልጅ ታገኛለች፡፡
ይብላኝ ለከሃዲው እንጂ ኢትዮጵያስ ከፍ ትላለች፡፡ አንድነታችንን ያፅናው፡፡
በታርቆ ክንዴ
Previous articleበምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የተመራ የልዑካን ቡድን በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጉብኝት እያካሄደ ነው።
Next articleዛሬ 5:30 ላይ “ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ክብር እቆማለሁ!” በሚል መሪ ሀሳብ ለሁለት ደቂቃ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ክብር በመቆም ፍቅራችንን የምንገልጽበት ሠአት እየደረሰ ነው፡፡