
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 07/2013 ዓ.ም (አብመድ) በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመክፈት የሀገር ክህደት የፈፀመውና ተከታታይ የህገ መንግሰት ጥሰቶችን ሲፈፅም የከረመው የአክራሪውን የህወሃት ፅንፈኛ ቡድን ለህግ ለማቅረብ እና የህግ የበላይነትን ለማስፈን ዘመቻ በመካሄድ ላይ መሆኑ ይታወቃል።
ህግ የማስከበር የህልውና ዘመቻው የውስጥ ጉዳይና በራስ አቅም መልክ ለማስያዝ የሚፈፀም በመሆኑ ምንም አይነት የውጭ ኃይል ጣልቃገብነት መኖር እንደሌለበት መንግስት አቋሙን ግልፅ አድርጓል።
ይህንኑ አቋም በማስረዳት የቀጣናው ሀገራት መንግስት የጀመረውን ህግና ህገ መንግስት የማጽናት ጥረት እንዲደግፉ ለማስቻል የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልዕክት የያዘና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራ የልዑካን ቡድን ወደ ተለያዩ የቀጣናው ሀገራት ጉብኝት ጀምሯል።
ኢዜአ እንደዘገበው ጉብኝቱ ከስድስት በላይ ሀገራትን የሚሸፍን መሆኑ ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እያለ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በዩጋንዳ ከህገወጡ ሕወሐት ጋር በሽምግልና ውይይት ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ በተለያዩ የዜና አውታሮች የቀረበው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ አስታውቋል፡፡