
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 05/2013 ዓ.ም (አብመድ) ‹‹ደካማ መግደል ባይችል ሞቶ ያሰድዳል›› ይላሉ አበው፡፡ ኢትዮጵያ ረጃጅም ሌሊቶችን አሳልፋለች፡፡ በዘመኗ ግን ሳይነጋ የቀረ ሌሊት የላትም፡፡ ረጅም ሌሊት በፅናት አንግታ ለዓለም ብርሃን አሳይታለች፡፡ አንደኛውን ረጅም ሌሊት ስታሳልፍ ሌላ ረጅም ሌሊት እየመጣባት ሁሉንም በፅናት አልፈዋለች፡፡ አሁን ምን አልባትም ደሮ ሊጮህ አካባቢ ካለው ረጅም ሌሊት ላይ ነው ያለች፡፡ የማለደ እንቅልፍ ሳታበዛ በስዓቱ እንደምታነጋው የብዙዎቹ እምነት ነው፡፡ እንቅልፍ ከጣላት ግን የሚቀጥለው ቀኗ የተበላሸ ነው የሚሆነው፡፡
በረጅም ሌሊት መተኛት መልካም በነበር፤ በረጅም ሌሊት መዋጋት ግን ከባድ ነው፡፡ ሌሊቱን ለማንጋት መዋጋት ስለሚጠይቃት በጨለማ ውስጥ ተዋግታ ከጥይት ጩኸት ማዶ ጎህ ስትቀድ ኖራለች፡፡ አሁንም ያንኑ ነው የምታደርገው፡፡
የሙዚቃው ንጉሥ ጥላሁን ገሰሰ ‹‹ አትቸኩይ ብዙ ምንድን ነው ጭንቀቱ
የረዘመ ሌሊት አይቀርም መንጋቱ፡፡ ›› ብሏል፡፡
ለዓመታት የረዘመው ሌሊት መንጋቱ የሚቀር አይመስልም፡፡ ሌሊቱ እስኪነጋ ድረስ ግን በጨለማ ውስጥ የሚጠፋ ነገር እንዳይኖር ጥንቃቄ ይሻል፡፡ ቢቻለው የራሱ ያልሆነን ታሪክ መወረስ ባይቻለው ግን ማፍረስ ከበርካታ መገለጫዎቹ መካከል አንዱ የሆነው ሕወሃት በተለይም የራሱን መልካም ታሪክ ጥሎ ማለፍ ቢሳነውም የቆዬውን መልካም ታሪክ እንዳያጠፋ ይሰጋል፡፡ በተለይ ደግሞ በአማራ ክልል የሚገኙ ታሪካዊ ሥፍራዎችን ለማጥቃት እስኪጋጋጥ መፍጨርጨሩ አይቀርም፡፡ አማራን አለፍ ሲልም ኢትዮጵያን ታሪክ አልባ ለማድረግ የሚቻለውን ሁሉ ያደርጋል፡፡ በዘመነ ስልጣኑ ራስ ደጀንን የሚያክል ተራራ ለመውሰድ ጥረት ያደረገው ሕወሃት በዘመነ ፍፃሜው ደግሞ ታሪኮችን አያጠፋም ማለት ሞኝነት ነው፡፡
የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት፣ የጎንደር አብያተ መንግሥታትና አብያተ ክርስቲያናት፣ የጣና ገዳማት፣ የጎዜ መስጂድና ሌሎችም በክልሉ የሚገኙ አያሌ ታሪካዊ ሥፍራዎችን ከሞቱ ጋር ይዞ ለመሞት ጥረት ሊያደርግባቸው የሚችሉ አካባቢዎች ናቸው፡፡ ትውልዱ አዲስ ታሪክ ለመጨመር የቀደሙትን መጠበቅ ግዴታ ውስጥ ገብቷል፡፡ ታሪክ መስራት ባይችል ታሪክ ማጥፋት ይቀነዋል፡፡ አልማዝ ከሆነ ታሪክ ውስጥ ሸክላ ፈልጎ ማጥላላት፣ ደግነት አፍርሶ ክፋት መሥራት፣ ፅኑ ሀገር ከፋፍሎ መንደር ማብዛት፣ ቀን አጉርሶ ሌሊት መውጋት፣ ስንዴ ለቅሞ እንክርዳድ መዝራት፣ ታማኝ አስሮ ሌባ መፍታት የመጣበት ታሪኩ ነውና፡፡
የሕዋሃት ዘመን ፀሐይ እየጠለቀ፣ የኢትዮጵያ የመከራ ዘመን ደግሞ እያለቀ ይመስላል፡፡ ፊት ለፊታቸው ብርሃንና ጨለማ የቀረባቸው በሚመስሉ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ግን የፊት ለፊታቸውን ለማግኘት በሚደረገው ጉዞ የሚወድቀው እንዳይበዛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡
በዚህ ወቅት የአማራ ክልል ታሪካዊና መንፈሳዊ ሥፍራዎች እንዴት እየተጠበቁ ይሆን ? የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኃይለ ኢየሱስ ፍላቴ ከአብመድ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
የህገወጡ የትህነግ ቡድን ሀገርን የማፈራረስና ታሪክን የማጥፋት አላማ ይዞ የሚሠራ ነው ብለውታል አቶ ኃይለ ኢየሱስ፡፡ ይህ ቡድን ኢትዮጵያን ካልመራሁ ማንም ሊመራት አይችልም የሚል አመለካከት ይዞ የሚንቀሳቀስ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡ ቡድኑ ሕዝብን ከማጥፋት በላይ የሕዝቦች የማንነት መገለጫ የሆኑ ቅርሶችን አፍርሶ ኢትዮጵያዊያንን ታሪክና ማንነት የሌላቸው እንዲሆኑ ለማድረግ የሚጥር ስለመሆኑም ነው የሚናገሩት፡፡
በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎችን ወደራሱ ለማድረግ ጥረት ሲያደርግ እንደነበር የገለፁት አቶ ኃይለ ኢየሱስ አሁን የመጨረሻው አማራጭ ቅርሶችን ለማጥፋት የማይፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም ነው ያሉት፡፡ ቡድኑ የጥፋት ተልዕኮ ሰጥቶ የበተናቸው ተላላኪዎች እንዳሉም አንሰተዋል፡፡
የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ቅርሶችን ከጥፋት ለመታደግ እየሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ የየአካባቢው ማሕበረሰብ ታሪክ አልባ እንዳይሆን ቅርሶችን እንዲጠበቅ እየተደረገ መሆኑንም ነግረውናል፡፡ ቅርሶችን ነቅቶ ለመጠበቅ ከአካባቢው ማሕበረሰብ፣ ከሚሊሻ አባላት፣ ከቅርስ አስተዳደርና ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን ጥብቅ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸውልናል፡፡
በቅርሶቹ አካባቢ ወዘ ልውጥ ሰው ሲታይ ጥቆማ በመስጠት በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ በክልሉ ምንም አይነት መዘናጋት እንደሌለም ተናግረዋል፡፡
ቅርሶችን መጠበቅ ለሌላ አካል የማይሰጥና በመዘናጋት የሚተው ነገር አለመኖሩንም አስገንዝበዋል፡፡
ማህበረሰቡ ቤተ እምነቶችና ታሪካዊ ቦታዎች የጥፋት ቡድኑ አላማዎች እንደሚሆኑ በመገንዘብ ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ በጉብኝት ሥም በመግባት አካባቢውን ለማጥቃትና ጥፋት ለማድረስ የሚንቀሳቀሱ አካላት ስለሚኖሩ አስጎብኝዎች የተለዬ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ወያኔ የጥፋት አቅሙ እየተዳከመ በመሆኑ የሚያሰራጫቸው የፕሮፓጋንዳ መረጃዎች እንደማያሸብርም ገልፀዋል፡፡
በክልሉ የተሟላ የጎብኝዎች አገልግሎት ለመስጠትም እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ዳግም እየተነቃቃ መሆኑን ያነሱት አቶ ኃይለ ኢየሱስ ከደህንነት ጥበቃ ጀምሮ፣ የተሟላ መስተንግዶ በመስጠት የጎብኚዎችን ጊዜ ማራዘም በሚቻልበት መንገድም ልዩ ልዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡ ቱሪዝም ላይ ያለው ጥንቃቄና ጥበቃ በወቅታዊ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ ቀጣይነት እንደሚኖረውም አስታውቀዋል፡፡
ዓይኖች ሁሉ መንፈሳዊና ታሪካዊ ቅርሶች ላይ ይዩ፤ አካባቢያቸውን በብስለት ይቃኙ፡፡
ዘጋቢ፡-ታርቆ ክንዴ