የአማራ ህዝብ ህገወጡን የትህነግ ቡድንን ለማስወገድ በሚደረገው እንቅስቃሴ ከሚያደርገው ድጋፍ ጎን ለጎን የልማት እና ማህበራዊ ሥራዎቹን እያከናወነ መሆኑን የክልሉ መንግስት አስታወቀ፡፡

155

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 04/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል መንግስት እና ህዝብ ለዘመናት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች እንዲዳከም የትህነግ ህገወጥ ቡድን ሲሰራ ቆይቷል፤ እየሰራም ይገኛል፡፡ ይህንን ህገወጥ ቡድን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ የሚወሰደውን የህግ ማስከበር ለሀገር ህልውና ዘመቻ በተለያየ መንገድ እየደገፉ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ወቅቱ የሚጠይቃቸው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስራዎች አለመቋረጣቸውን የአማራ ክልል መንግሥት አስታውቋል፡፡

የክልሉ መደበኛ የስራ እንቅስቃሴዎች በከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ልዩ ስምሪት ተሰጥቷቸው በትኩረት በመስራት ላይ እንደሚገኙ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩንኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ ተናግረዋል፡፡

የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ክልል ልዩ ሃይል እና ሚሊሻ አባላት የጋራ ጠላት የሆነውን ጁንታ ከስሩ ለማሰወገድ እየወሰዱ በሚገኙት የህግ ማስከበር ለሀገር ህልውና ዘመቻ ህዝቡ በተለያዩ መንገዶች በድጋፍ እየገለፀ ነው ብለዋል፡፡

ከድጋፉ ጎን ለጎን የደረሱ ሰብሎችን የመሰብሰብ፣ የመስኖ ልማት ስራዎችን የማከናወን እና የስራ ዕድል ፈጠራዎች በመደበኛ አደረጃጀቶች በትኩረት እየተሰራበት መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

የጤና እና የትምህርት እንዲሁም ሌሎች የማህበራዊ ዘርፎችም ልዩ ትኩረት የተሰጠባቸው ስራዎች መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

ህገወጡ ህወሓት ባለፉት ዓመታት በክልሉ ያሰማራቸው ተላላኪዎች ብሔርን ከብሔር እና ሃይማኖትን ከሃይማኖት በማጋጨት የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ ስለሚሯሯጡ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን በንቃት መከታተል እንደሚገባቸው አቶ ግዛቸው አሳስበዋል፡፡

ኅብረተሰቡም ከፖሊስ እና ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በጋራ በመሆን አካባቢውን በመጠበቅ ብሎም ፀጉረ-ለውጥ ሰው ሲያጋጥም ፈጥኖ ለፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት መተባበር እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በክልሉ በተከናወኑ ልዩ ልዩ የፀጥታ ማስከበር ስራዎች ተጠርጣሪ ግለሰቦች፣ የጦር መሳሪያዎች እንዲሁም ለወንጀል አገልግሎት ሊውሉ የሚችሉ ቁሳቁሶችም እንደተያዙም አስታዉቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleከአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተላለፈ መልዕክት
Next articleከብልጽግና ፓርቲ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ