
ለድርድር የሚቀርብ አካል ቢኖር እሱም ክህደት እንደፈፀመ እንሚቆጠር ነው የህግ ባለሙያው ያስገነዘቡት፡፡
ህወሃት የፈፀመው ድርጊት በህገ መንግስቱና በኢፌዴሪ የወንጀል ህግ ለእርቅና ድርድር ከማይቀርቡ ወንጀሎች እንደሚመደብም የህግ ባለሙያው ጠበቃና የህግ አማካሪው ገበያው ይታየው ገልፀዋል።
ባሕር ዳር፡ ህዳር 03/2013 ዓ.ም (አብመድ) በሰሜን ዕዝ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የፌዴራል መንግስት እየወሰደው ያለውን የህግ ማስከበር ሥራ እና አጠቃላይ የተፈጸመውን ወንጀል አስመልክቶ የህግ ባለሙያ አነጋግረናል፡፡ ጠበቃ እና የህግ አማካሪ ገበያው ይታየው እንደገለጹት በሀይል፣ በዛቻ፣ በአድማ ወይም ሕገ ወጥ በሆነ ማንኛውም መንገድ የፌዴራሉን ወይንም የክልሉን ህገ መንግስት ያፈረሰ፣ በሕዝብ ኑሮ ላይ ከፍተኛ ቀውስ ያደረሰ እንደሆነ አድራጊው በዕድሜ ልክ እስራት ወይንም በሞት እንደሚቀጣ በ1996 ዓ.ም በወጣው የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 238 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ ተቀምጧል፡፡
ይህን አጥፊ ቡድን በማንኛውም መንገድ መደገፍ በኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 251 ከ20 ዓመታት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ወይም ነገሩ ከባድ ከሆነ በእድሜ ልክ እስራትና ሞት እንደሚያስቀጣም የህግ ባለሙያው አስረድተዋል።
በወንጀል ህጉ አንቀጽ 240 እንደተመለከተው ደግሞ የጦር መሳሪያ ይዞ የእርስ በዕርስ ጦርነት ማስነሳት፣ በመንግስት ላይ ማመጽ ከአስር ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት ሊደርስ በሚችል ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣ መቀመጡንም ባለሙያው ነግረውናል፡፡
ድርጊቱ በሕዝብ ደኅንነት ወይንም ኑሮ ላይ ከፍተኛ ቀውስ ያስከተለ እንደሆነ በዕድሜ ልክ እስራት እንደሚያስቀጣም ባለሙያው ገልጸዋል፡፡ በዚህም ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጀምሮ ትህነግ የራሱን ጦር በማዘጋጀት እና ሌሎች ቡድኖችን እና ግለሰቦችን በማደራጀት በፌዴራል ስርዓቱ ላይ አደጋ ለመጣል ግልጽ ጦርነት ከፍቷል።
በፌዴራል ስርዓቱ ላይ አደጋ መጣል ብቻ ሳይሆን የፌዴራል ስርዓቱ በሚያስተዳድራቸው ተቋማት ላይ ጭምር ጦርነት ከፍቶ ጉዳት አድርሷል፡፡
በወንጀል ህጉ 251 ላይ እንደተመላከተውም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይንም የኢትዮጵያን ጥቅም እንዲያስከብር በግልጽ አደራ የተጣለበት አካል ከጠላት ጋር በመተባበር የወገን ተዋጊዎችን ለጠላት ያጋለጠ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሃሳብ፣ በገንዘብ፣ ጋዜጠኛ ሆኖ በመዘገብ፣ ጸሐፊ ሆኖ በመፃፍ እና ሀገርን ሊያፈርሱ በሚችሉ ውይይቶች የተሳተፈ አካል ከ20 ዓመታት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣም ተናግረዋል።
የብዙ ሰዎች ሕይወት ካለፈ እና የንብረት ውድመት ከተከሰተ ደግሞ በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይንም በሞት እንደሚያስቀጣ ተቀምቷል፡፡ እንደ ህግ ባለሙያው ማብራሪያ ጦርነቱ በሚካሄድበት ወቅትም ማንኛውም ሰው አስቦ ህግን በመጣስ ከሀገር የወጣ ወይንም የገባ እንደሆነ በወንጀል ያስጠይቃል፤ ሌላው በወንጀል ህጉ አንቀጽ 247 ላይ እንደተመላከተው ማንም ሰው አስቦ የመከላከያ አልባሳትን፣ መሳሪያን እና በመሳሰሉ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት እንዲሆን በታቀደ ማንኛውም ድርጅት ላይ የሚፈጸም ወንጀል የሀገር መከላከያ ሀይልን በመጉዳት ወንጀል ያስጠይቃል፡፡
በተለይም ደግሞ ሲቪል ያልሆኑ ግለሰቦች፣ የሀገር መሪዎች፣ ክልል የሚያስተዳድሩ ግለሰቦች ከታጠቁ አካላት ጋር ከተባበሩ እና ከተመሳጠሩ በወንጀል ያስጠይቃቸዋል፡፡ በተለይም ድርጊቱ የተፈጸመው የጦር መሳሪያ በመያዝ ከሆነ ደግሞ የሀገር መክዳት ወንጀል እንደተፈጸመ ይቆጠራል፡፡ በዓለም ወታደራዊ የወንጀል ፍርድ ቤት እንደሚያስጠይቅም ነው የህግ ባለሙያው የገለጹት፡፡ በዚህ ድርጊት የተሳተፈ አካልም እስከ ሞት እንደሚያስቀጣው ባለሙያው አብራርተዋል፡፡
የተፈጸመው ድርጊትም በህገ መንግስቱ ወይንም በወንጀል ህጉ ለእርቅ እና ድርድር እንደማያስቀርብ የህግ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡ ባለሙያው እንደገለጹት መከላከያን መድፈር፣ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን መጣስ፣ በንጹሃን ዜጎች ላይ ጦርነት ማወጅ በእርቅ እና በድርድር የሚከስሙ የወንጀል ድርጊቶች አለመሆናቸው በህገ መንግስቱ ወይንም በወንጅል ህጉ ተቀምጠዋል፡፡ መንግስት ድርጊቱን የመሩ፣ በድርጊቱ የተሳተፉ፣ በስብሰባ ወይም ጦርነትን ያወጁ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋል እና ለህግ ማቅረብ እንደሚገባው ጠቁመዋል።
ትህነግ የህፃናት መብት ኮንቬንሽንን በመጣስ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትን ጭምር ለጦርነት በመመልመል ዓለም ዓቀፍ ህግን ጭምር መጣሱንም ባለሙያው አስረድተዋል፡፡ በዚህ ወቅትም ማኅበረሰቡ ከማንኛውም የወንጀል ድርጊት እና ቡድን ራሱን ማራቅ፣ በገንዘብ እና በሃሳብ ከመተባበር መቆጠብ እንደሚገባው የህግ ባለሙያው አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m