
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 03/2013 ዓ.ም (አብመድ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዲሱ የበጀት ቀመር አስተዳደር፣ አተገባበር፣ የበጀት ክፍፍል መረጃ አያያዝና አጠቃቀም ዙሪያ በአዳማ ዛሬ እየመከረ ነው።
የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ እንደገለፁት ከክልል መንግስታት ገቢና የወጪ ፍላጎት ጋር የተጣጣመ የበጀት ቀመር ተግባራዊ ተደርጓል።
የመድረኩ ዓላማ የቀመሩ አስተዳደርና አተገባበር ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ አንፃር እየተተገበረ መሆኑን ለመገምገም መሆኑንም ተናግረዋል፤ ይህም ጤናማና ውጤታማ የበጀት ድጎማ ቀመር እንዲኖር ከማድረጉም ባለፈ ዘመን ተሻጋሪ ሆኖ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።
በስራ ሂደትም በየጊዜው እየተተገበረና ውጤታማነቱ እየተገመገመ ይሄዳል ያሉት አፈ ጉባኤው ክልሎች ፍትሃዊ የገቢ ክፍፍል እንዲኖራቸው ለማስቻል በ2012 ዓ.ም ተግባራዊ መደረጉን ነው የተናገሩት። በዚህም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ትግበራ ጥሩ ውጤት መገኘቱን የገለጹት አፈ-ጉባኤው “ይሄም በክልሎች መካከል ፍትሃዊና የተመጣጠነ ልማት እንዲረጋገጥ ያስችላል” ብለዋል።
የፌዴራል መንግስት ለክልሎች የሚሰጠው የበጀት ድጎማ ቀመር ውጤታማነትን ለማረጋገጥ የመረጃ አያየዝና አጠቃቀም ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።“ለዚህም ወቅታዊ፣ ትክክለኛና ጥራት ያለው የመረጃ አደረጃጀትና አያያዝ ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል” ብለዋል።
በመረጃ አያያዝ፣ አቀራረብና አጠቃቀም ሊኖር የሚችለውን ክፍተት ለማስወገድ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናት እየተካሄደ ነው፤ በዚህም ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል፣ የመሰረተ ልማት ስርጭትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ጭምር እንደሚጠቅምም አፈ-ጉባዔው ተናግረዋል።
የበጀት ድጎማና የገቢዎች ክፍፍል ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ፀሐፊ አቶ ሃይሉ ኢፋ በበኩላቸው “ገቢን በአግባቡ ለመሰብሰብና ክልሎችም በአግባቡ እንዲያስተዳድሩት በሚያመነጬት ኢኮኖሚ ልክ እንዲደርሳቸውና ለምን ዓላማ እንዳዋሉት የሚያረጋግጥ ነው” ብለዋል።
ምክር ቤቱ የመረጃ ስርዓት ዘርግቶ ከመከታተል አንፃር ሰፊ ክፍተት እንደነበረበት የጠቀሱት ጸሐፊው አዲሱ የበጀት ቀመር ተግባራዊ ከመሆን ጋር ተያይዞ የሚዘረጋው የመረጃ ስርዓት ችግሩን ከመሰረቱ የሚያቃልል መሆኑንም አመላክተዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ በ1989 ዓ.ም የነበረውን የበጀት ድልድል ቀመር ከአጠቃላይ በጀት 70 በመቶ የሚሆነው ለፌዴራል፤ 30 በመቶ ለክልሎች ድጎማ የሚሰጥ ሲሆን አዲሱ ቀመር 50 በመቶ ለፌዴራል፤ 50 በመቶ ደግሞ ለክልሎች መሰጠቱ ተገልጿል።