“ህወሐት ሁለት መሳሪያ አላት፤ ክህደት እና ውሸት” አቶ መስፍን ደሳለኝ

466

ባሕር ዳር፡ ህዳር 03/2013 ዓ.ም (አብመድ) ምድር በርካታ የከፉ ሁነቶችን ተቀብላ ሸኝታለች፡፡ መፈጠርን የሚያስጠሉ ተግባራት በዘመናት መካከል ሁሉ በምድር ላይ ተስተናግደዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን የጀግንነት ታሪካቸው ሁሉ አውራ የሆነው የአድዋ ድል በዓለም ሕዝብ ዘንድ ቅቡል ካደረጉት ጉዳዮች መካከል አንዱ ከአውደ ውጊያው ድል ባለፈ ለጠላቶቻቸው የሚያሳዩት ርህራሄ እና ሰብዓዊነት ነበር፡፡

ጣሊያኖች ከመቀሌ ምሽጋቸው በሴት ባለመላዋ የጦር ጥበብ እቴጌ ጣሐይቱ እንዳልሆነ ሆነው ሲወጡ ከጀርባቸው ጥይት ያርከፈከፈባቸው አልነበረም፡፡ ይልቁንም ያ የጥቁር መሪ ለብርታታቸው እህል ውኃ፣ ለጓዛቸው አጋሰስ መድቦ እና “ስታገግሙ ትገጥሙናላችሁ” ብሎ ወደ ወገኖቻቸው ሸኝቶ ልኳቸዋል፡፡ ይህንን ለማመን የሚከብድ በራስ መተማመን እና የርህራሄ ጀብድ ምናልባትም በሃገር ውስጥ ጸሃፊ ቢነገረን አለማመናችን በብዙ መልኩ ምክንያታዊ በሆነ ነበር፡፡

ነገር ግን ይህንን የሐበሻ ጀብዱ እንዳየው ከትቦ የነገረን አዶልፍ ፓርለሳክ ነው፡፡ ይህ ሕዝብ “ጦርነት አንፈልግም” ሲል “ጦርነት አንችልም” ወይም “ጦርነትን እንፈራለን” ማለቱ አልነበረም፡፡ ጦርነት ትርፍ አልባ ንግድ መሆኑን ቀድሞ ስለሚረዳ እንጅ፡፡
በወገኑ ያልተጠበቀ ክህደትና ጥቃት የተፈጸመበት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከትሪፖሊ እስከ ኮሪያ፣ ከመቋዲሾ እስከ ጁባ ለሠላም ዘብ በመቆም ገናና ስም አለው፡፡

የአፍሪካ ቀንድ የፀጥታ እና ሠላም ደጀንም ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ይህንን ሐይል ከጀርባው ሆኖ መውጋት ባንዳነት ካልሆነ የጦር ስልት አዋቂ ወይም ጀግና አያሰኝም፡፡ በሠላም ጊዜ የልማት፣ በጭንቅ ወቅት ደግሞ መከታ እና ሐይል የሆነን ሠራዊት ባልጠበቀው መንገድ መውጋት የጠላቶቹን አርቆ አለማየት አመላካች ነው፡፡

የሚገርመው ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ለጦርነት ቀን ቆርጠው ቦታ መርጠው ካልሆነ ትጥቅ የፈታ ጠላታቸውን በድንገት አያጠቁም፡፡ መሰል የሐበሻን ክብር እና ስም የማይመጥኑ ተግባራትን መመልከት ግን የታሪክ አንድ አካል እየሆነ መጥቷል፡፡

ከሰሞኑ ትህነግ የፈጠረው ክህደት የሚያስገርመው በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከዚህ ዓይነቱ ኋላቀር አስተሳሰብ መውጣት አለመቻሉ እንደሆነ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር መስፍን ደሳለኝ ተናግረዋል፡፡ ትህነግ ገና ተሓህት በሚል ስያሜ ለትጥቅ ትግል እየተንቀሳቀሰ ሳለ በወንድሞቹ ላይ የፈፀማቸውን አረመኔያዊ ተግባራት ላየ ከዚህ የተሻለ አይጠብቅም ነው ያሉት፡፡

የቀድሞው የትህነግ መስራች እና ነባር ታጋይ የኋላ ዘመኑ አፈንጋጩ ሰው ገብሩ አስራት ‹‹ሉዓላዊነት እና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕሰ በፃፉት መጽሐፋቸው ትህነግ በብዙ እኩይ ተግባራት ያለፈ ድርጅት እንደሆነ ነግረውናል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ተሓህት ለአንድ ዓላማ የሚታገለውን ግገሓትን ያስወገደበት መንገድ አሳዛኝም አስገራሚም ነበር፡፡

አቶ ገብሩ አስራት እንደሚሉት ግገሓቶች የነበራቸውን ሠራዊት ከተሓህት ሠራዊት ጋር ለማዋሃድ ተዘጋጅተው እያሉ የተሓህት መሪዎች የግገሓትን ኃይል በእንቅልፍ ላይ እንዳለ በቁጥጥር ስር ለማዋል ሴራ ጠነሰሱ፡፡ ይህን ሴራ ተግባራዊ ያደርግ ዘንድም እያንዳንዱ የተሓህት ታጋይ ከግገሓት ታጋዮች ጋር ከተገናኙ በኋላ አንድ ለአንድ አብሮ እንዲተኛ እና ጎህ ሊቀድ ሲል ምልክት ሲሰጠው አብሮት የተኛውን የግገሓት መቆጣጠር እንዳለበት ሚስጥራዊ ምልክት ተላለፈ፡፡

ጎህ ሲቀድ ትጥቅ የፈቱትን እራቁታቸውን ሲለቋቸው እምቢ ያሉትን እንደነ የማነ ገብረመስቀል አይነት ጀግኖችን ደግሞ የጥይት በረዶ አዘነቡባቸው፡፡ ከደርግ ውጭ ትጥቅ ሊያስፈታን የሚችል ኃይል አይኖርም ብለው ለነፃነት ትግል እና ለተመሳሳይ ዓላማ የወጡት የግገሓትን ኃይሎች በወንድሞቻቸው ተከድተው እንደተበተኑ አቶ ገብሩ አስራት ጽፈዋል፡፡ “ህወሀት ሁለት መሳሪያ አላት ክህደት እና ውሸት” የሚሉት አቶ መስፍን አሁን ግን ሁለቱም መሳሪያዎች ዘመን ያለፈባቸው እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ መስፍን ማብራሪያ ትህነግ በድርድር ስኬታማ ታሪክ ኖሮት አያወቅም፤ ከዚህ ይልቅ ለጥቅሙ እና ለስልጣኑ ይቀናቀኑኛል ብሎ ያሰባቸውን ከጀርባ ወግቶ የማስወገድ ክህደት ልምድ ባለቤት ነው፤ በሃገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈጠረው ክህደትም ከጥልቅ ፍርሃቱ የመነጨ ነው፡፡ እየተወሰደ ባለው የህግ ማስከበር ሥራ ክፉኛ የተደናገጠው ዘራፊ ቡድን በንፁሃን ላይ ጥቃት እንደሚፈጽም የትዴፓ ምክትል ሊቀ መንበሩ ተናግረዋል፡፡ የመጀመሪያ ሕዝቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ጥቃቶች ከተፈጠሩ ደግሞ ነገሮችን በትዕግስት በመመልከት እለተሞቱን ማፋጠን እንጂ ትህነግ በምትፈልገው መንገድ ስሜታዊ ሆኖ የርስ በዕርስ ግጭት መግባት አያስፈልግም ነው ያሉት፡፡
የትግራይ ሕዝብም የተጫነበትን የባርነት ቀንበር ከትከሻው ለመጨረሻ ጊዜ ለማውረድ ጊዜው አሁን መሆኑን አውቆ ከመንግስት ጎን ሊቆም እንደሚገባ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዶ/ር ደብረጸዮን ገብረሚካኤልን ጨምሮ የሌሎችን ግለሰቦች ያለመከሰስ መብት አነሳ፡፡
Next articleየጅማ እና አጋሮ ከተሞች ነዋሪዎች መንግስት በትግራይ ክልል የሚያካሂደውን የህግ ማስከበር ስራ እንደሚደግፉ ገለጹ፡፡