ወንበዴው እና ስግብግቡ የሕወሓት ቡድን በመከላከያ ሠራዊት ላይ ያደረሰውን ጥቃት የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።

253

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 03/2013 ዓ.ም (አብመድ) የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ መሐመድ ሰልፉ በተካሄደበት የጅግጅጋ ስታድየም ባደረጉት ንግግር ስግብግቡ ጁንታ አፀያፊ ተግባር በሶማሌ ሕዝብ እና በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ያሳረፈው ቁስል ሳይሽር በቅርቡ የሃገር አለኝታ በሆነው የመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመው ተግባርም እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።

የሰልፉ ዓላማም ወንበዴው የሕውሓት ቡድን በሥልጣን ዘመኑ ያደረሰውን ግፍ እንዲሁም ከሰሞኑ በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመውን ጥቃት እና አሁንም እያደረገ ያለውን የክህደት ተግባር ለማውገዝ መሆኑን አቶ ሙሰጠፌ አስታውቀዋል።

ተጠያቂነት የማይሰማው ይህ ወንበዴ ቡድን በዘር፣ በሃይማኖት እና በብሔር እያደረገ ያለውን የመከፋፈል ሥራም እንደሚያወግዙት ነው ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ የተናገሩት።

ስግብግቡ የሕወሓት ቡድን ለ27 ዓመታት በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ከባድ በደል አድርሷል ያሉት የሰላማዊ ሰልፉ ተሳታፊዎች፣ በቅርቡ በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ የፈፀመውን አስነዋሪ ጥቃት አውግዘዋል። ይህ ቡድን የፈፀመው ተግባር አስነዋሪ ከመሆኑም በላይ ድርጊቱ ችግሮችን በሰላም እና በውይይት ይፈታል የሚለውን ተስፋቸውን ያሟጠጠ እንደሆነም ገልጸዋል።

የመከላከያ ሠራዊት እያደረገ ያለውን የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራ እንደሚደግፉ የገለጹት ተሳታፊዎቹ የእናት ጡት ነካሽ የሆኑትን የቡድኑን አባላት ለሕግ የማቅረብ ሥራ ያለምንም ድርድር ተጠናክሮ እንዲቀጠል ጠይቀዋል።

ቡድኑ በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ የፈፀመው ዓይነት ተግባሩን ማስቆም የሚቻለው የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ብቻ እንደሆነም እምነታቸው መሆኑን አስገንዝበዋል። የዚህ ቡድን አባላት በመላው ኢትዮጵያዊ ላይ ከፍተኛ በደል ማድረሳቸውን በተለይ ደግሞ በሶማሌ ክልል በሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከልም መከፋፈል እንዲመጣ ሲሠሩ እንደቆዩ መናገራቸውን ኢብኮ ዘግቧል፡፡

Previous articleየፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የትህነግን ጥፋት ዝረዝር ጉዳዮች ለሕዝብ እንደራሴዎች በማቅረብ በሽብርተኝነት እንዲፈረጅ ማድረግ እንደሚገባው የአማራ ክልል ርዕስ መስተዳደር የህግ አማካሪ አሳሰቡ፡፡
Next articleየህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዶ/ር ደብረጸዮን ገብረሚካኤልን ጨምሮ የሌሎችን ግለሰቦች ያለመከሰስ መብት አነሳ፡፡