በህገወጡ የትህነግ ቡድን ላይ ህግ የማስከበር ርምጃ እየፈፀሙ ለሚገኙት ለሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ ለአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና ለሚሊሻ አባላት የሚደገው ድጋፍ እንደቀጠለ ነው፡፡

371

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 02/2013 ዓ.ም (አብመድ) ህገወጡ ትህነግ የሃገር መከታ በሆነው የመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት በዘራፊው ቡድኑ ላይ እያከናወነ ያለውን ህግ የማስከበር ርምጃ እየፈጸሙ ላሉት የመከላከያ ሰራዊት፣የአማራ ልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት ሕዝቡ አጋርነቱን በተግባር እያሳዬ ይገኛል።

በራያ ግንባር ለሚገኘው ሰራዊት የሰሜን ሸዋ ዞን ህዝብ የበግና የበሬ ሰንጋዎችን ለቆቦ ከተማ አስተዳደር አስረክቧል፤ የምግብ ቁሳቁሶችንም ድጋፍ አድርገዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ታደሰ ገ/ጻዲቅ እንዳሉት የዞኑ ሕዝብ የትህነግን የጥፋት እርምጃ በማውገዝ በቁጭት ከመንግስት የህግ ማስከበር እርምጃ ጎን መሰለፉን ተናግረዋል። የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ በዞኑ ለመከላከያ ሰራዊቱና ለልዩ ኃይሉ ደም የመለገስ ተግባር እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል። በዚህ ሰብዓዊ ተግባር በዞኑ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆችም ተሳታፊ መሆናቸውንም አስታዉቀዋል፤ የህገወጡን ትህነግ የረጅም ዓመታት የተዛባ የፖለቲካ አካሄድን ተረድተው ከመንግስት ጎን እንደቆሙም በተግባር አሳይተውናል ብለዋል።

በዘራፊው የትህነግ ጁንታ ላይ በህግ ማስከበር ርምጃ ለተሰማራው ሰራዊት የምግብ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ እንደ ክልል በተከፈተው የገቢ ማሰባሰቢያ ሂሳብ ቁጥር 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የዞኑ ህዝብ ድጋፍ ማድረጉንም ዋና አስተዳዳሪው አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ ዜና የወልድያ ከተማ አስተዳደር ሕዝብ ለመከላከያ ሰራዊቱና ለአማራ ልዩ ኃይል የምግብ ግብዓቶችንና የበሬ ሰንጋዎችን ደግፏል። ጽንፈኛው የትህነግ ቡድን በህግ ተጠያቂ እስኪሆን ድረስም ከመንግስት ጎን እንደሚሰለፉ ነው የከተማዋ ነዋሪዎች ለአብመድ የገለጹት።

ህገወጡ ትህነግ ሕዝቦችን በመከፋፈልና በንጹሐን ደም ሲነግድ ኖሯል ያሉት ነዋሪዎቹ ትህነግ ለትግራይ ጠበቃ በመምሰል የሚያራምደው የተዛባ ፕሮፖጋንዳ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
የወልድያ ከተማ ከንቲባ መሐመድ ያሲን የከተማዋ ህዝብ ከ540ሺህ ብር በላይ በማዋጣት ከሰራዊቱ ጎን መሆኑን በተግባር አረጋግጧል ነው ያሉት። በቀጣይም የትህነግ ስግብግብ ጁንታ ለህግ እስከሚቀርብ ድጋፋቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን የተሁለደሬ ወረዳ ህዝብም ለሰራዊቱ ድጋፍ አድርጓል።

ዘጋቢ፡- ስማቸው እሸቴ

Previous articleየህወሃት ጁንታ የኤርትራ መከላከያ ሰራዊትን መለዮ ለታጣቂዎች በማልበስ ኤርትራ እንደወረረችው በመግለጽ ሕዝብን እያደናገረ መሆኑን መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።
Next article“የሕወሃት ወንጀለኞች በአዲስ አበባ እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ፍርሃትን ለመንዛትና እና የሽብር ጥቃትን ለማድረስ አስፈፃሚ መረብ አቋቁመዋል” የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ