
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 02/2013 ዓ.ም (አብመድ) “ሁመራና አካባቢው ሙሉ ለሙሉ በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር ውሏል” ሲሉ የአገር መከላከያ ሰራዊት የኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ተናግረዋል፡፡
ሰራዊቱ በአሁኑ ወቅት ከሁመራ እስከ ሽራሮ ያለውን ቦታ በማጥቃት የተለያዩ ስፍራዎችን በቁጥጥር ስር እያዋለ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
ሰራዊቱ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ ሰዎች ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ የእርዳታ ድርጅቶች ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር ተነጋግረው ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።
የህወሃት ጁንታ በአልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የኤርትራ መከላከያ ሰራዊትን መለዮ በማዘጋጀት ላደራጃቸው ታጣቂዎች በማልበስ ኤርትራ እንደወረረች በመግለጽ ሕዝብን እያደናገረ እንደሆነም አስታውቀዋል።
በዚህ የተቀናበረ ድራማ ሕዝቡ ሳይታለል ለመከላከያ ሰራዊቱ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡