
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 02/2013 ዓ.ም(አብመድ) በበይነ መረብ ወይም ኢንተርኔት የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎች ከህግ ማስከበሩ እርምጃ ጋር ምንም አይነት ቀጥተኛ ግንኙነት የሌላቸው መሆኑን ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል፡፡ የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውንም ገልጿል፡፡
ከሐሰተኛ መረጃዎቹ መካከል ቢቢሲ በፎቶ አስድግፎ የተወሰኑትን አውጥቷል፡፡ መንግስት የሚወስደውን የአየር ጥቃት ለመከላከል የሚያስችል ኤስ-400 ሩሲያ ሰራሽ ሚሳኤል ትህነግ እንደተጠቀመ ተደርጎ መረጃ ተሰራጭቷል፡፡ ነገር ግን ይላል ቢቢሲ በትንታኔው ይህ ተጠቃሽ ሚሳኤል ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን አልመግባቱን ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል ትህነግ በመቀሌ እና አካባቢው የአየር ድብደባ መፈፀሙን ገልፆ አንድ የጦር ጀት መትቶ እንደጣለም መረጃ አሰራጭቶ ነበር፡፡ ቢቢሲ በዘገባው እስካሁን በመንግስት ህግ አስከባሪዎች እና በትህነግ ቡድን መካከል በተደረገው የተኩስ ልውውጥ ተመትቶ የወደቀ የጦር ጀት የለም ነው ያለው፡፡
በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ‹‹የትግራይ ልዩ ኃይል መትቶ የጣላት ተዋጊ ጀት›› በሚል አንድ የወደቀ ጀት ምስል ያጋራሉ ያለው ቢቢሲ ምስሉ ግን በ2018 የኢራኑ ፕረስ ቴቪ በየመን ተመትቶ የወደቀውን የሳውዲ አረቢያ ተዋጊ አውሮፕላን ምስል መሆኑን አስታውቋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቴክኒክ ችግር ምክንያት ከአንድ ዓመት በፊት ከአዲስ አበባ እንደተነሳ ብዙ ሳይጓዝ የወደቀውን እና ከ150 በላይ ሰዎች ህይዎት ያጡበትን ፎቶ እንደሚጠቀሙም ቢቢሲ ጠቁሟል፡፡
የጤና ሚኒትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ.ር) በትዊተር ገፃቸው እንደለጠፉት ተደርጎ የተወሰደው እና ‹‹በጦርነቱ ወታደሮች ሳኒታይዘር፣ ማክስ እና እርቀታቸውን ጠብቀው እንዲዋጉ መልዕክት አስተላልፈዋል›› በሚል የተለጠፈው መልዕክት ሐሰተኛ ነበር ብሏል ቢቢሲ በማብራሪያው፡፡