
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 02/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ ሰልፉን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም መላው የክልላችን ህዝብ፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም የመንግሥት ሠራተኞች ህገ ወጡ የትህነግ ቡድን ያደረሰውን ግፍ እና የሀገር ክህደት ወንጀል ለመላው ዓለም በምንችለው ሁሉ ለማሳወቅ የሰልፉ ተሳታፊ አንድንሆን ጥሪ እናቀርባለን ብለዋል፡፡
ህዝቡ ህገወጡ ትህነግ ቡድን እያደረሰ ያለውን ግፍ በአደባባይ ለመቃወም በተለያየ መንገድ ጥያቄውን ሲያቀርብ የቆየ መሆኑንም አቶ ግዛቸው ጠቁመዋል፡፡
የሰልፉ ዓላማ ህገ ወጡ የትህነግ ቡድን እየፈጸመው ያለውን ግፍና በሀገር መከላከያ ሰራዊታችን ላይ ያደረሰውን ክህደት ለመላው ዓለም ለማሳወቅ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ሰልፉ የሚካሄደውም በባህር ዳር፣ ፍኖተ ሰላም፣ እንጅባራ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ብርሃን፣ ኮምቦልቻ፣ ደሴ እና ደብረ ታቦር ከተሞች ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከእነዚህ ከተሞች ውጭ ባሉ የክልሉ ከተሞች ሰልፉ የማይካሄደው ህገ ወጡን የትህነግ ቡድን በህግ ቁጥጥር ሥር ለማዋል በሚደረገው ውጊያ ልዩ የጸጥታ ጥበቃ ስለሚያፈልጋቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሰልፉ ነገ ጠዋት 2፡30 ተጀምሮ በአጭር ጊዜ ይጠናቀቃል፤ በተዋቀረው የሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴ እና በጸጥታ ኃይል ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለት መሆኑንም ማስታወቃቸውን የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ዘግቧል፡፡