‹‹ ራስን በማምለክ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ ከፍተኛ የኃይል መጠን ያለውን ኤሌክትሪክ ያስጨብጣል፤ ህገወጡ ሕወሃት በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረገው ጥቃትም ይህ ነው›› በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የስነ ልቦና መምህር አውግቸው ሽመላሽ

282

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 1/2013 ዓ.ም (አብመድ) የስነልቦና ጦርነት በተለያዩ መንገዶች ሥራ ላይ ማዋል እንደሚቻል የስነ ልቦና ምሁራን ይገልፃሉ፤ ለዚህ ደግሞ ትልቁ መሳሪያ የሰው ልጅ ጭንቅላት ነው። የብዙ ሰዎችን ጭንቅላት ያሳመነ አስተሳሰብ አሸናፊ መሆኑ አይቀሬ ነው፤ አንድ አካል ጠላት ብሎ ያሰበውን አካል ለማሸነፍ በአስተሳሰብ በልጦ መገኘት ያስፈልጋል፤ በአስተሳሰብ በልጦ ለመገኘት ደግሞ ምክንያታዊነት ብቻውን በቂ አለመሆኑን ነው የስነ ልቦና ምሁራን የሚገልጹት፤ ከምክንያታዊነት በተጨማሪ ስሜቶችን መቆጣጠር እንደሚገባም ይገልፃሉ።

አሸናፊ ስነልቦና ያለው አካል ስሜቶቹን የሚቆጣጠር፣ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንኳን መንፈሱ የተረጋጋ ነው፤ ስለሆነም ለማሸነፍ በተረጋጋ የአዕምሮ ሁኔታ ላይ መገኘት ይገባል፡፡ የስነ ልቦና ምሁራን እንደሚሉት አምባገነን ሥርዓትን ማሸነፍ የሚቻለው የሥርዓቱ አራማጆች ወደ እብደት የተጠጋ የስነልቦና ቀውስ ውስጥ ሲገቡ ነው፤ ያኔ ውሳኔዎቻቸው ሁሉ የጭንቀት ይሆንና በስህተት ላይ ስህተት ይጨምራሉ፤ ከጭንቀት ብዛት የራሳቸውን ወዳጆች ሳይቀር ያጠፋሉ።

በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የስነ ልቦና ትምህርት ክፍል መምህር አውግቸው ሽመላሽ እንደገለጹት ህገወጡ ሕወሃት ለራሱ በእብሪት የተሞላ፣ እኔ ያልኩት ትክክል ብሎ የሚያስብ፣ ራሱን የሚያመልክ ቡድን እንደሆነ ነው፡፡ አንድ ቡድን ከራስ ወዳድነት አልፎ የቡድን አምልኮ ይዞ ሲመጣ ግን የማይሞከር ነገር ይሞክራል፡፡ ሕወሃትም ራሱን በማግዘፉና ማምለክ ደረጃ ላይ በመድረሱ ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ መከታ እና አለኝታ በሆነው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ፈፅሟል ብለዋል፡፡

‹‹ራስን ማምለክ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ ከፍተኛ የኃይል መጠን ያለውን ኤሌክትሪክ ያስጨብጣል፡፡ ህገወጡ ሕወሃት በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረገው ጥቃትም ይህ ነው›› ብለዋል የስነ ልቦና ምሁር፡፡

የስነ ልቦና የበላይነትን ለመቀዳጀት ወሬዎችን፣ አሉባልታዎችንና ማሳሳቻዎችን በሬድዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በበራሪ ወረቀቶች፣ ከሰው ወደ ሰው እና በማሕበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት መንዛት ደግሞ የተለመደ ነው፡፡ ህወሃትም የስነ ልቦና የበላይነትን ለመቀዳጀት ባቋቋመው ሚዲያ እና በማህበራዊ ሚዲያ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ማሕበረሰቡም ይህ የህገወጡን ሕወሃት የውሸት ወሬ የህዝብን ድጋፍ ለማግኘት አስቦ የሚነዛ መሆኑን በመረዳት ትክክለኛውን መረጃ ከትክክለኛው ሚዲያ ማግኘት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ህዝቡም አካባቢውን በመጠበቅ በግልጽ እና በህቡዕ ሊሰነዘር የሚችለውን ጥቃት ሊከላከል እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ

Previous articleግለሰቧ በአማራ ክልል ሁለተኛ ጤና ጣቢያ አስገንበተው አስረክበዋል፤ ሦስተኛውን ለማስገንባትም በዝግጅት ላይ ይገኛሉ፡፡
Next article“እየሞትንም ቢሆን እናሸንፋለን!” የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ