የደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደር ለመከላከያ ሰራዊት ፣ ለአማራ ክልል ልዩ ሃይል እና ሚሊሻ አባላት የሰንጋ፣ የበግና የፍየል ድጋፍ አደረገ።

924

ባሕር ዳር፡ ህዳር 01/2013 ዓ.ም (አብመድ)
የደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደር የትህነግ ወንበዴ ቡድን በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ህግን ለሚያስከብሩ የሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ክልል ልዩ ሃይልና ሚሊሻዎች ከጎናቸው መሆኑን ለመግለፅ ሰሞኑን ከ1 ሚሊዮን በላይ የሚያወጡ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል።

በዛሬው ዕለት ደግሞ የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር 12 ሰንጋ፣ ላይጋይንት ወረዳ 9 ሰንጋ ፣ አንዳቤት ወረዳ 5 ሰንጋ እንዲሁም መካነ እየሱስ ከተማ አስተዳደር 81 በግና ፍየሎችን ድጋፍ አድርገዋል።

የደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪና የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ደሳለኝ አልታሰብ የደብረታቦር ከተማ የንግዱ ማህበረሰብ ከ5 መቶ ሺህ ብር በላይ በማሰባሰብ ከመከላከያ ፣ ከአማራ ልዩ ሃይልና ከሚሊሻ አባላት ጎን መሆናቸውን ለመግለፅ 12 ሰንጋ እና 350 ደርዘን እሽግ ውሃ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተናገሩት አቶ ደሰላኝ የህግ ማስከበሩ ሥራ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግና አካባቢውን ነቅቶ እንዲጠብቅ አሳስበዋል።

ጦርነቱ ኢትዮጵያን የማዳን ስራ ነው ያሉት አቶ ደሳለኝ የኢትዮጵያ ህዝብ በዘር እና በሃይማኖት ሳይለያይ የበኩሉን ድጋፍ በማድረግ ጦርነቱ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ህብረተሰቡ ወደ ልማት እንዲመለስ ከመከላከያ፣ ከአማራ ልዩ ሃይልና ከሚሊሻ አባላት ጎን መሰለፍ ይገባል ብለዋል።

የመካነ እየሱስ ከተማ አስተዳድር ምክር ቤት አፈ ጉባኤና የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ጌጤ ገላው በበኩላቸው የትህነግ አምባ ገነን ቡድን በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰውን ጥቃት ለመከላከል ውጊያ እያደረጉ ለሚገኙ ለመከላከያ ሃይል፣ ለልዩ ሃይል እና ለሚሊሻ አባላት 81 በግና ፍየል ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ድጋፉን ወደፊት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለፁት አቶ ጌጤ በየአካባቢው የሚገኙ የሚሊሻ አባላት እና ህብረተሰቡ አካባቢውን ነቅቶ መጠበቅ እንዳለበትም ተናግረዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳደሪ ቀለምወርቅ ምህረቴ የትህነግ ቡድን በሃገር ላይ ያሳየውን ክህደት ተከትሎ የሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ክልል ልዩ ሃይልና የሚሊሻ አባላት ህግ እያስከበረ ነው ብለዋል።

“በህግ ማስከበር ሥራ የሚገኙ የፀጥታ አካላት ህዝባዊ ደጀን ያስፈልጋቸዋል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ድጋፍ ላደረጉ ወረዳዎች እና የከተማ አስተዳደሮች የሰራዊቱ ደጀን በመሆናቸው በዞኑ አስተዳደር ስም ምስጋና አቅርበዋል። በቀጣይም ዞኑ በሁሉም መስክ የሚያስፈልገውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ከሃዲዎችን ለመያዝ መንግስት በሚያደርገው የህግ ማስከበር ስራ ህብረተሰቡ የሰራዊቱ ደጀን በመሆን የቀደምት አባቶቻችንን ታሪክ መድገም እንደሚገባም ነው አቶ ቀለምወርቅ ያስገነዘቡት።

ዘጋቢ ፦ አማረ ሊቁ – ከደብረ ታቦር

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleለሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለአማራ ልዩ ኃይልና ለሚሊሻ አባላት የሚደረገው የደም ልገሳ ቀጥሏል፡፡
Next articleግለሰቧ በአማራ ክልል ሁለተኛ ጤና ጣቢያ አስገንበተው አስረክበዋል፤ ሦስተኛውን ለማስገንባትም በዝግጅት ላይ ይገኛሉ፡፡