ለሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለአማራ ልዩ ኃይልና ለሚሊሻ አባላት የሚደረገው የደም ልገሳ ቀጥሏል፡፡

592

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 1/2013 ዓ.ም (አብመድ) “ለጀግናችን እንለግስ ደማችን” በሚል መልዕክት በባሕር ዳር የሙሉዓለም ባሕል ማዕከል የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ደም ለግሰዋል፡፡

የህወሃት ጽንፈኛ ቡድን በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የፌዴራል መንግሥት የህግ ማስከበር ሥራ እየሰራ ነው፡፡

ህገወጡን ሕወሃት ወደ ሕግ ለማቅረብ የሕይወት መስዋዕትነት እየከፈሉ ለሚገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለአማራ ልዩ ኃይልና ለሚሊሻ አባላት የሚደረገው የተቀናጀ ድጋፍ ቀጥሏል፡፡

በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለአማራ ልዩ ኃይልና ለሚሊሻ አባላት የደም ልገሳ መርሀ ግብሮች እየተደረጉ ነው፡፡ በዛሬው ዕለትም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ደም እየለገሱ ነው፡፡

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የምዕራብ ዕዝ የኦርኬስትራ ኃላፊ ሻምበል ታዘበው ንጋቱ የሃገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ አባላት መስዋዕትነት እየከፈሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

“ሠራዊቱ ደጀን ያስፈልገዋል” ያሉት ሻምበል ታዘበው የኪነጥበብ ባለሙያዎች ሙያቸውን ለሀገር አንድነትና ፍቅር ማዋል እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡ “እውነት ሁልጊዜም አሸናፊ ናት፤ እነርሱ በውሸት የፖለቲካ አቅጣጫ ነው ወደ ግጭት ያመሩት፤ በሕዝባችን እተማመናለሁ፤ ሕዝቡ በፍቅርና በሠላም መኖር ይፈልጋልም” ብለዋል ሻንበሉ፡፡

ሕዝቡ ከሚያደርገው የተቀናጀ ድጋፍ ጎን ለጎን ንፁሃንን ከወንጀለኞች የመነጠል ሥራ መሠራት እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡

በሙሉዓለም ባሕል ማዕከል ተዋናይት ሙሉ ብስራት “ለመከላከያ ደሜን በመለገሴ ደስታዬ ከፍ ያለ ነው፤ በጦርነቱ ተገደው የገቡ የትግራይ ልዩ ኃይል አባላትም ወንድሞቻችን ናቸው፤ ደም ያስፈልጋቸዋል” ብላለች፡፡

በሙሉዓለም ባህል ማዕከል የባሕል ፕሮግራሞች ዝግጅትና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር ሙላት ዋለ እንደ ኪነጥበብ ባለሙያ ግንባር ቀደም መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል፤ የደም ልገሳውም ለሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለአማራ ልዩ ኃይልና ለሚሊሻ አባላት ከጎናቸው መሆናችንን ለማሳዬት ያለመ ነው ብለዋል፡፡ “ሀገር በጥባጩ ቡድን ተለይቶ እንዲመታ ከሀገር መከላከያ ጎን እንሰለፋለን” ነው ያሉት፡፡

በሙሉዓለም ባሕል ማዕከል የባህልና ዘመናዊ ሙዚቃ ዳይሬክተርና የዝግጅቱ አስተባባሪ ሰለሞን ታደሰ ከሙሉዓለም ባሕል ማዕከል በተጨማሪ የግሽ ዓባይ ባሕል ቡድን፣ የፖሊስና የምዕራብ እዝ ኦርኬስትራ አባላትና ሌሎች መሳተፋቸውን ነው የገለፁት፡፡

ደም ልገሳው የኪነጥበብ ባለሙያው ደጀን መሆኑን ለማሳዬት ያለመ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፤ ግንባር ድረስ ሄዶ ሠራዊቱን ለማነቃቃትም ዕቅድ ይዘው እየሰሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

በባሕርዳር ደም ባንክ ነርስ ገነት አስፋው የደም ልገሳው ዝግጅት ከወትሮው በተለዬ መነቃቃት ማሳዬቱን ጠቁመዋል፡፡ በሁለት ቀን ብቻ ከአንድ ሺህ በላይ ዩኒት ደም መለገሱንም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡-ታርቆ ክንዴ

Previous articleህገወጡን የህወሃት ቡድንን ለመደምሰስ በግንባር እየታገሉ ለሚገኙ ለመከላከያ ሰራዊት፣ ለአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ አባላት የሚውል የደም ልገሳ መርሃ ግብር በወልድያ ከተማ እየተከናወነ ነው፡፡
Next articleየደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደር ለመከላከያ ሰራዊት ፣ ለአማራ ክልል ልዩ ሃይል እና ሚሊሻ አባላት የሰንጋ፣ የበግና የፍየል ድጋፍ አደረገ።